ሪፖርት| ቢጫ ለሻሾቹ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተው መትረፋቸውን አረጋግጠዋል

ሪፖርት| ቢጫ ለሻሾቹ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተው መትረፋቸውን አረጋግጠዋል

ቢጫዎች በሰመረ ሀፍታይ ብቸኛ ግብ አዞዎቹን በማሸነፍ በሊጉ መቆየታቸውን አረጋገጠዋል

አስቀድመው ከሊጉ መውረዳቸውን ያረጋገጡትን አዞዎቹን ከቢጫ ለባሾቹ ያገናኘው ተጠባቂው ጨዋታ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ውጤቱ ማስመዝገብ ግዴታ የሆነባቸው ወልዋሎዎች እንዳሰቡትም ሆኖላቸው ጨዋታው ገና ሰባተኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከራሳቸው ሜዳ ክፍል የተሻገረውን ኳስ ሀፊዝ ኮንኮኒ በግንባሩ ጨርፎ ሲያሻግራት ብሩክ ባይሳ ኳሱን ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ በሰራው ስህተት ኳሱ አልፎበት ሰመረ ሀፍታይ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ሳጥን ውስጥ በመግባት በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

በነፃነት ሲጫወቱ የነበሩት አዞዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ ከተጋጣሚያቸው በላይ ወደ ፊት ተጠግቶ ሙከራዎችን እያደረጉ የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በተለይም ሳጥን ውስጥ ተጨራርፎ የወጣውን ኳስ ኤፍሬም ታምራት አግኝቶ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ያወጣባተው እና የቆመ ኳስ ተቀባብለው ጄሮም ፈሊፕ አክርሮ መትቶ በድጋሚ ግብ ጠባቂው ያገደባቸው አደገኛ ሙከራ ይታወሳል። ወልዋሎዎችም በአንድ አጋጣሚ ተጨማሪ ግብ ሊሆን የተቃረበ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን የቆመ ኳስ ተሻምቶ ኪሩቤል ሳጥን ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ ባይመልስበት መሪነታቸውን አጠናክረው መውጣት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ አዞዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ማጥቃት በማጋደል የአቻነት ግብ ፍለጋ ከፍተኛ ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። ኤፍሬም ታምራት በጥሩ ሁኔታ መትቶት በግቡ ቋሚ ብረት የተመለሰበት የቆመ ኳስ ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የተቃረበ እጅግ አደገኛ ሙከራ ነበር።
​በአንፃሩ ወልዋሎዎች ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ የሆነችውንና እጃቸው የገባችውን ውጤት ይዘው ለመውጣት ወደ ኋላ አፈግፍገው በጥንቃቄ ተከላክለዋል፤ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ሞክረዋል። ጨዋታውም በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ለቢጫ ለባሾቹ በሊጉ ለመቆየት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ሦስት ነጥብ በማስገኘት ተቋጭቷል።