የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 37ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሁለተኛው ቀን ጨዋታዎች ይቀጥላል። ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ተጠባቂ የሆኑ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ድሬዳዋ ከተማ
በ46 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠው ሀዲያ ሆሳዕና ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙትን ብርቱካናማዎቹን ይገጥማል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ወልዋሎን 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፎ በሊጉ ያረጋገጠው ቡድኑ ትልቁ ጥንካሬው በተለይ በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተው የኋላ መስመር አደረጃጀቱ መሆኑ ይታወቃል። ተጋጣሚያቸው ካለበት የወራጅ ቀጠና ስጋት የተነሳ ከፍተኛ ማጥቃትና ጫና ፈጥሮ እንደሚገባ ስለሚጠበቅም ጨዋታው ቀላል አይሆንም። ነብሮቹ የዛሬውን ጨዋታ በድል ለመወጣት በመጨረሻ ሳምንት ያሳዩትን የማሸነፍ ስነ-ልቦና መድገም እንዲሁም የፊት መስመራቸውን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በ38 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ያለውን ጠባብ የመትረፍ ዕድል ለመጠቀም ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል። በመጨረሻ ሳምንት ሸገር ከተማን 2ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወሳኝ 3 ነጥብ ቢያስመዘግብም አሁንም ወራጅ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በሊጉ ለመትረፍ ያለውን ጠባብ ዕድል ለማለምለም ድል ማድረግ እንዲሁም የቅርብ ተፎካካሪዎቹን ነጥብ መጣል ይጠብቃል። በዚህ አማራጭ የሌለው የሞት ሽረት ጨዋታም
ባለፈው ሳምንት ያሳየውን የማጥቃት ውጤታማነት ማስቀጠል ይኖርበታል።
ቡድኖቹ ከዚህ በፊት በሊጉ አስራ ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ነብሮቹ በአምስቱ ሲያሸንፉ ብርቱካናማዎቹ አራት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀዋል። 27 ግቦችንም መረብ ላይ ያሳረፉ ሲሆን ሀዲያዎች 13 ግቦችን ድሬዎች ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ሽረ ምድረ ገነት
በደረጃ ሰንጠረዡ በ46 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በወራጅ ቀጠና የሚገኘውን ሽረ ምድረ ገነት ይገጥማል። በመጨረሻው ጨዋታ በመቻል ጋር 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት የተሸነፈው ቡድኑ ወደ ድል ጎዳና ለመመለስ ይጫወታል። ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም ባለፈው ሳምንት የታየበትን የፊት መስመር ድክመት ማረምና የሚፈጠሩትን የግብ ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም ይኖርበታል።
በ39 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ሽረዎች በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ምንም ግብ 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት በመለያየት አንድ ነጥብ ያሳካው ቡድኑ ለመትረፍ ያለውን ዕድል ለመጠቀም ዛሬ ድል ማድረግ በእጅጉ ያስፈልገዋል። በ16ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው አዳማ ከተማ በአራት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘውና ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ በቀዳሚነት በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመሩ ማሻሻል ግድ ይለዋል።
ሦስት ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ መድን በሁለቱ በማሸነፍ የበላይነት ያሳየ ሲሆን ቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል። በግንኙነታቸው 7 ግቦች መረብ ላይ ያረፈ ሲሆን መድን ስድስቱን ሲያስቆጥር ሽረ ምድረ ገነቶች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥረዋል።

