ኢትዮጵያ ቡና ስብስቡን እያጠናከረ ይገኛል

ኢትዮጵያ ቡና ስብስቡን እያጠናከረ ይገኛል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድንቅ ብቃት ያሳየው ሩዋንዳዊ ኮከብ ወደ ቡናማዎቹ ያመራል

ከቀናት በፊት ዶ/ር ለይኩን ታደሰ የአካል ብቃት አሰልጣኝ እንዲሁም አምባዬ በፍቃዱ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት እና በዝውውር መስኮቱ የነባር ተጫዋቾች ውል በማራዘም እና አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድናቸውን በማጠናከር ላይ የሚገኙት በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ደግሞ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሩዋንዳ ሊግ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው አጥቂ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል። ቡናማዎቹን ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ታይባ ምቦኒዩምዋሚ ነው።

በሀገሩ ክለብ ማሪንስ በነበረው የመጨረሻ ዓመት ቆይታ በሀያ ሰባት ጨዋታዎች አስራ ሰባት ግቦች አስቆጥሮ አምስት የጎል አቅርቦት በማድረግ በድምሩ ሀያ ሁለት የግብ አስተዋፅዖ ያደረገው ይህ ተጫዋች በBk Pro league የውድድር ዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዕጩዎች ተካቶ የነበረ ሲሆን ከስኬታማው የውድድር ዓመት በኋላም ኢትዮጵያ ቡና የዛምያው ክለብ ዛናኮን አሸንፎ ተጫዋቹን የግሉ ማድረግ ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በBk Pro league የውድድር ዓመቱ ምርጥ 11 ከተካተት ታይባ ምቦኒዩምዋሚ በተጨማሪ ደግሞ በአማካይ ቦታ ለሚሰለፈው ዴሞክራቲክ ኮንጓዊ ማቩንጉ ምቤሉ የሙከራ ዕድል እንደሰጡ ለማወቅ ተችሏል።