በአፍሪካ መድረክ ሀገራችንን የሚወክለው ሲዳማ ቡና ለፌዴሬሽኑ በብሔራዊ ቡድን ጥሪ በቀረበላቸው ተጫዋቾች ዙርያ ያስገባው ደብዳቤ በእጃችን ይገኛል።

በአሰልጣኝ ዩሐንስ ሳሀሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጪው መስከረም ወር ለሚያደርጋቸው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝግጅት በቅርቡ ለ39 ተጫዋቾች ጥሪ መደረጉ ይታወቃል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከትናንትና ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል የተሰባሰቡ ሲሆን ዝግጅታቸውን ዛሬ የሚጀምሩ ይሆናል።
ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ከሲዳማ ቡና ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸው ብርሃኑ በቀለ፣ አቤል ያለው፣ ያሬድ ባዬ፣ መስፍን ታፈሰ፣ ደግፌ አለሙ እና ቢንያም በላይ ብሔራዊ ቡድኑን እንደማይቀላቀሉ ታውቋል።
ይህም የሆነው በዚህ ወር መጨረሻ ሲዳማ ቡና ሀገራችን በመወከል በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ለሚኖርበት ቅደም ማጣርያ ጨዋታ ዝግጅቱን እያደረገ ሲሆን የቡድኑ ወሳኝ የሆኑት ስድስቱ ተጫዋቾች ቡድኑን የማይቀላቀሉ ከሆነ በቡድኑ ዝግጅት ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ከግምት በማስገባት ለጊዜው ተጫዋቾቹን እንደማይልክ እና በፊፋ ህግ መሰረት ጨዋታው መቃረቢያ ላይ አስፈላጊውን ነገሮች ለማድረግ እንደሆነ ሰምተናል።
ሲዳማ ቡናም ይህንን አቋሙን በግልፅ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ማስገባቱን ሶከር ኢትዮጵያ በእጇ የገባውን ደብዳቤ አይታ አረጋግጠለች። ፌዴሬሽኑም የክለቡን ጥያቄ መቀበሉን በደብዳቤ ማሳወቅን ያረጋገጥን ሲሆን ተጫዋቾቹም የአሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌን ስብስብ ሳይቀላቀሉ በክለባቸው ዝግጅት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ታውቋል።

