በአሰልጣኝ በሽር አብደላ እና ሀላባ ከተማ መሀል ንፋስ ሳይገባ አልቀረም

ሀላባ ከተማ ለብዙ ዓመታት ወደ በፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ የሚያደርውን ጉዞ መግቢያ በር ላይ እየደረሰ ሳይሳካለት ከቀረ በኋላ ዘንድሮ በአሰልጣኝ በሽር አብደላ እየተመራ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማደግ የዓመታት ህልሙን ማሳካቱ ይታወሳል።
በርበሬዎቹ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ በሚያደርጉትን ተሳትፎ ጠንካራ ቡድን ይዘው ለመቅረብ ከአሰልጣኝ በሽር ጋር በጋራ ወደ ዝውውሩ በመግባት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ቢቆዩም በቅርብ ቀናት ግን በሁለቱም አካላት ንፋስ ሳይገባ እንዳልቀረ ሰምተናል። አሰልጣኙ ቀደም ብለው በክለቡ አካሄድ ዙሪያ ቅሬታ እንዳላቸው እና ነገሮች እንዲስተካከሉ ጥያቄ ማቅረባቸው የሰማን ሲሆን ክለቡም ከማሰልጠን ፍቃድ ጋር በተያያዘ በስራው መቀጠል እንደማይችል እና በአሰልጣኞች ቡድን ውስጥ ተቀላቅሎ እንዲቀጥል ጥያቄ እንዳቀረበለት ታውቋል። በዚህ ምክንያት በሁለቱም አካላት የነበረው መቀራረብም ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ በስተመጨረሻ ለመለያየት እንደተቃረቡ አውቀናል።
አሰልጣኝ በሽር ዓብደላ እና ሀላባ ከተማ የነበራቸውን እህል ውሀ ወደ ማብቃቱ የተቃረበ ሲሆን ክለቡም አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ንግግር እንደጀመረ ታውቋል። ሶከር ኢትዮጵያም በዚህ ዙሪያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች እየተከታተለች የምታቀርብ ይሆናል።

