የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን የሴካፋ ሻምፒዮንስ ሊግ የመክፈቻ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን በዛሬው እለት የመክፈቻ ጨዋታውን ያደርጋል። በሩዋንዳ ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም በሚካሄደው በዚህ የምድብ ለ የመጀመሪያ መርሐግብር ከጅቡቲዋ ኤፍሲ ኡጄኮ (FC Ujeco) ጋር ይገናኛል። የዞኑ አዘጋጅ ሀገር ሩዋንዳ በሆነችበት የዘንድሮው ውድድር የ2024 የሴካፋ ሻምፒዮን የሆኑት የንግድ ባንክ እንስቶች ባለፉት ቀናት ኪጋሊ የገቡ ሲሆን ዘንድሮም የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ እንዲሁም የውድድሩ ባለክብር ለመሆን ሙሉ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የንግድ ባንክ የዛሬ ተጋጣሚ ኤፍሲ ኡጄኮ (FC Ujeco) የጅቡቲ የሴቶች ሊግ አሸናፊ በመሆን የዘንድሮውን የሴካፋ ውድድር የተቀላቀሉ ሲሆን በክልላዊ እና አህጉራዊ መድረኮች በቂ ልምድ የሌለው ቡድን ነው። ይህ ጨዋታ ለንግድ ባንክ በምድቡ ውስጥ ያለውን የበላይነት ቀድሞ ለመያዝ እና ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፍ እድሉን ለማስፋት እጅግ ወሳኝ ሚና አለው።
ጨዋታው በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ በሩዋንዳ ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይደረጋል።

