ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 2 | የአዳማ ከተማ መለያ ጉዳይ

ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 2 | የአዳማ ከተማ መለያ ጉዳይ

በአዲሱ የውድድር ዘመን ሁለተኛ የትኩረት አጀንዳችን የአዳማ ከተማ መለያ ሆኗል!

ለአዲሱ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመሩ ሊጉን ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመግጠም የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በጨዋታው ይዘው ከወጡት ሦስት ነጥብ ባሻገር የመለያቸው ጉዳይ ትኩረትን የሳበ ነበር።

ለወትሮው ከተለመዱት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ (ነጭና ቀይ) መለያዎች በተለየ በአዲስ ትጥቅ አቅራቢ ድርጅት አረንጓዴ መለያ ሲጠቀሙ ያስተዋልናቸው አዳማዎች ከመለያቸው በስተጀርባ የሰፈረው የተጫዋቾች ስያሜ የተፃፈበት መጠን ግን በጣም አስገራሚ ነበር።

በመለያው ጀርባ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ስም የሰፈረበት መጠን (Font Size) ለወትሮው በመለያዎች ላይ ከተለመደው በእጅጉን የጎላ ሲሆን በተጫዋቾች ጀርባ ላይ ካለው ቁጥር ጋር ያለው ምጥጥን (Proportion) በራሱ ፍፁም የተዛባ እንደነበር በግልፅ ማስተዋል ይቻላል።

ምንም እንኳን እንደ ሀገር በዚህ ረገድ የተቀመጡ ደንቦች ባይኖሩም ለአብነት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በመለያዎች ጀርባ ላይ የሚሰፍረው የተጫዋቾች ስም መጠን ከ7.5 ሴንቲሜትር መብለጥ እንደሌለበት የሚደነግግ ሲሆን የአዳማ ከተማ መለያ ላይ ግን ያለው ከዚህም ከፍ ያለ ስለመሆኑ ማስተዋል ችለናል።

የአዳማን ለአብነት አነሳን እንጂ ለዕይታ የሚያዳግቱ ፣ ከመለያው ቀለም ጋር ፍፁም በተቀራረቡ ቀለሞች የሚፃፉ ስምና ቁጥሮች ፣ ከጀርባ የታጨቁ ፅሁፎችን ጨምሮ በዚህ ረገድ ብዙ ክፍተቶችን መመልከት በሊጋችን ብርቅ አይደለም።

እንደ ሊግ አክሲዮን ማህበሩ በተጫዋቾች ስም አፃፃፍ  (Typeface) ፣ መጠን (Font Size) ፣ አቀማመጥና መሰል ተያያዥ ጉዳይ ላይ ወጥ አሰራር ለመከተል የሚያስችል ህግጋትን ተግባራዊ እስካላደረገ ድረስ መሰል የተዘበራረቁ ነገሮች መመልከታችን አይቀሬ በመሆኑ መሰል ጉዳዮች በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።