ሉሲዎቹ ሩዋንዳን በድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ሶስተኛ ዙር ማጣሪያ አለፉ

ሉሲዎቹ ሩዋንዳን በድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ሶስተኛ ዙር ማጣሪያ አለፉ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2028 ኦሊምፒክ የሴቶች እግር ኳስ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር በአቻ ውጤት ተለያይቶ፣ በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ሶስተኛ ዙር ማጣሪያ ማለፍ ችሏል።

በአብዩ አረጋሽ

ሉሲዎቹ የመልስ ጨዋታውን በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ 10፡00 ላይ ከሩዋንዳ ጋር አድርገው በአቻ ውጤት ያጠናቀቁ ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ በኪጋሊ 1 ለ 0 ድል ማድረጋቸው ለቀጣዩ ዙር ማለፋቸው ወሳኝ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ የሉሲዎቹ ዋና አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የቡድኑ ዋነኛ ዓላማ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ እንደነበርና ይህንንም ማሳካታቸውን ገልጸዋል።

አሰልጣኙ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናቸው ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳሳየና በተጋጣሚው ላይ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠሩን በመጥቀስ፣ በአጠቃላይ የቡድናቸውን አቋም አወድሰዋል።

በጨዋታው ወቅት ስለተደረጉት ቅያሪዎች በተጠየቁበት ወቅትም በሜዳ ላይ የፈለጉትን ነገር ማግኘት ባለመቻላቸው ቅያሪዎቹን ማድረጋቸውን ገልጸው የወሰዱት ውሳኔ ትክክለኛ እንደነበር አስረድተዋል።

በጨዋታው ላይ ስለተሰጠው የኦፍሳይድ ውሳኔ አስተያየት እንዲሰጡ ሲጠየቁም የዳኛውን ውሳኔ ማክበር እንደሚገባ በመግለጽ ተመሳሳይ ውሳኔ በቡድናቸው ላይ ቢወሰንም እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

አሰልጣኝ ቻለው በመጨረሻም በጨዋታው የታዩ ስህተቶችን በመተንተንና በማረም በቀጣይ የተሻለ አቋም ያለው ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

በዚህም ሉሲዎቹ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ጉዟቸውን በድል በመቀጠል፣ ወደ ሶስተኛ ዙር ማጣሪያ ተሸጋግረዋል።