ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ጅማሮ እያበሰረ ያለው የዘመናዊነት እርምጃ ለሌሎች ክለቦችም ትልቅ ትምህርት ይዞ የመጣ በመሆኑ የትኩረታችን ማዕከል ሆኗል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ አብዛኞቹ ክለቦች በባህላዊ አስተዳደር፣ በወረቀት ላይ በተመሰረተ አሰራር እና ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሮችና በመንግስት በጀት ላይ ጥገኛ ሆነው የቆዩ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቢዘገዩም ከሌሎቹ አንፃር ቀድመው የነቁ እጅግ ውስን ክለቦች ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ዘመናዊ የኢ-ኮመርስ (E-commerce) የትጥቅ ሽያጭ፣ የዲጂታል አባልነት እና የኢንተርፕራይዝ ሀብት ማኔጅመንት (ERP) አሰራር ለመሸጋገር የሚያደርጉት ጥረት የሊጉን ተወዳዳሪነት እና ተቋማዊ እድገት ወደ አዲስ ደረጃ እያሸጋገረው ይገኛል። በተለይ ከሰሞኑን ቅዱስ ጊዮርጊስ ራሱን ዘመኑን በዋጀ መንገድ ለማሻሻል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እጅግ መልካም የሚባል ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ግንባር ቀደም ባለታሪኩ እና በርካታ ደጋፊዎችን ያፈራው ቅዱስ ጊዮርጊስ አጠቃላይ የክለቡን አስተዳደራዊ እና ፋይናንሳዊ አሰራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቀየር ያለመ ሰፊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት እየጀመረ መሆኑን ከሊጉ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የሜዳ ውጪ ጉዳዮች ትኩረታችን ጋር አያይዘን ለማቅረብ ወደናል።
ክለቡ በዚህ አዲስ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ዘመናዊ ኦፊሴላዊ ዌብሳይት፣ የኢንተርፕራይዝ ሀብት ማኔጅመንት (ERP) ሶፍትዌር ስርአት እና የዲጂታል የአባልነት መመዝገቢያ ፕላትፎርም በጥምረት ስራ ላይ እያዋለ ይገኛል። ይህም የፈረሰኞቹን አሰራር ግልጽነት ባለው ፈጣን እና ዘመናዊ በሆነ የዲጂታል መሰረት ላይ የሚያስቀምጥ ተቋማዊ ሽግግር ተደርጎም ይወሰዳል።
ክለቡ ይፋ ያደረገው አዲሱ ዌብሳይት ለደጋፊዎች፣ ለብዙሃን መገናኛዎች እና ለንግድ አጋሮች ሰፊ የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው። የዋናው ቡድን፣ የሴቶች እና የታዳጊ ቡድኖች የጨዋታ ፕሮግራሞች፣ ውጤቶች እና የደረጃ ሰንጠረዦች በየጊዜው በዌብሳይቱ እየዘመኑ እንደሚሄድ የሚጠበቅ ሲሆን የቡድኑ አባላት ዝርዝር መረጃ፣ የተጫዋቾች ግልጽ ስታቲስቲክስ እና ታሪካዊ ሰነዶች በዲጂታል መዝገብ ቤት መልክ እንደሚደራጁም ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ የሚያወጣቸው ይፋዊ መግለጫዎች፣ የተጫዋቾች ዝውውር ዜናዎች እና የቪዲዮ ይዘቶች በቀጥታ በዌብሳይቱ እንደሚሰራጩ ይገመታል።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የክለቡ ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በቴክኖሎጂ ታግዘው ከክለባቸው ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ የሚያስችል ስርአትም የተዘጋጀ ሲሆን ደጋፊዎች በስልካቸው ወይም በኮምፒውተራቸው አማካኝነት ምዝገባ በመሙላት የዲጂታል የአባልነት መታወቂያ ያገኛሉ። ወርሃዊ እና ዓመታዊ የአባልነት ክፍያዎች በሀገር ውስጥ በተለያዩ የክፍያ አማራጮች እና በሀገር ውጭ በክሬዲት/ዴቢት ካርዶች በኩል በቅጽበት እንደሚፈፀምና ደጋፊዎች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እና ድጋፍ መሰረት ያደረጉ ልዩ ልዩ የጥቅማጥቅም ደረጃዎች (Platinum, Gold, Silver) በአበርክቷቸው እንደሚቀመጥ ተመላክቷል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ዘመናዊ እርምጃ በዚህ ሳያበቃ የክለቡን የውስጥ አሰራር እና አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል የሚቀይረው የERP ስርአት ስራ ላይ እየዋለ እንደሆነ ተጠቁሟል። በዚህም የክለቡ ገቢ፣ ወጪ፣ የስፖንሰርሺፕ ገቢዎች እና በጀት በአንድ ማዕከላዊ ሶፍትዌር ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ተብሏል። በዚህም የንብረት እና የሰው ሀብት አስተዳደር በተደራጀ መንገድ የመረጃ ደህንነቱ በተጠበቀ ስርዓት እየተሰነደ ይገኛል። ታዲያ ይህ የዲጂታል መንገድ በሜዳ ላይ ከሚመጣው የስፖርት ስኬት ባልተናነሰ መልኩ ክለቡን በጠንካራ የፋይናንስ እና የአስተዳደር መሰረት ላይ የሚያቆመው እንደሚሆን ይታመናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ እያስጀመረው ያለው አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ክለቡን ከባህላዊ የስፖርት ማኅበርነት ወደ ዘመናዊ፣ ራሱን ወደቻለ እና ተወዳዳሪ የስፖርት ተቋም የሚያሸጋግር ከፍተኛ ተቋማዊ ፋይዳ ያለው ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው። አብዛኞቹ የሀገራችን ክለቦች ሙሉ በሙሉ በመንግስት በጀት ወይም በጥቂት ባለሀብቶች ድጋፍ ላይ የተንጠለጠሉ ቢሆንም ይህ አዲሱ የዲጂታል አባልነት እና የክፍያ ስርአት ክለቡ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ሚሊዮኖች ደጋፊዎቹ ቀጥተኛ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ ወርሃዊ ገቢ እንዲሰበስብ እድል ይፈጥርለታል። ከዚህ በተጨማሪም ስራ ላይ የዋለው የኢንተርፕራይዝ ሀብት ማኔጅመንት (ERP) ሶፍትዌር የክለቡን ገቢና ወጪ፣ የስፖንሰርሺፕ ውሎችን፣ ንብረቶችን እና የተጫዋቾች ኮንትራት በማዕከላዊ የቴክኖሎጂ ስርአት በመቆጣጠር የፋይናንስና የአስተዳደር ግልጽነትን ያረጋግጣል ፤ ይህም የስፖንሰሮችንና የኢንቨስተሮችን እምነት በከፍተኛ ደረጃ የመገንባት አቅም አለው።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መንገድ ለሌሎች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ትልቅ ተሞክሮ እና የማንቂያ ደወል ነው። ለብዙ ዓመታት በባህላዊ አሰራር እና በከተማ አስተዳደሮች በጀት ላይ ጥገኛ ሆነው የቆዩት የሀገራችን ክለቦች ይህንን የቴክኖሎጂ መንገድ በመከተል የፋይናንስ ነፃነታቸውን ማረጋገጥ እና አስተዳደራዊ አሰራራቸውን ማዘመን እንዳለባቸው ያሳያል።
የሊጉ ክለቦች ከዚህ ሊወስዱት የሚገባው ዋናው ትምህርት የደጋፊዎቻቸውን አቅም በዲጂታል አባልነትና በክፍያ ስርአቶች ወደ ዘላቂ ገቢ መቀየር ይቻላል የሚለውን እውነታ ነው። በተጨማሪም የERP አሰራርን መተግበር አስተዳደራዊ እና የፋይናንስ ብክነትን በመቀነስ የስፖንሰሮችን እና ኢንቨስተሮችን እምነት ይገነባል። በመሆኑም የሊጉ ክለቦች የጊዮርጊስን እርምጃ እንደ ተራ ዜና ሳይሆን ራሳቸውን ወደ ዘመናዊ የንግድ ተቋምነት በመቀየር በረጅም ጊዜ ዘላቂነታቸውን የሚያረጋግጡበት ብቸኛ መንገድ አድርገው ሊወስዱት ይገባል።

