በአብዩ አረጋሽ
ነጌሌ አርሲዎች ሸገር ከተማን 2 ለ 1 በማሸነፍ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ግስጋሴያቸው ሲያስቀጥሉ ሀላባ ከተማዎችም ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 በማሸነፍ አንሰራርተዋል

ነገሌ አርሲ ለ ሸገር ከተማ
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ቀን 9:00 ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ ነገሌ አርሲ ሸገር ከተማን 2ለ1 በማሸነፍ ሊጉን መምራት ጀምሯል።
ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ በ40ኛው ደቂቃ ላይ ከቤ ብዙነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ሀቢብ ከማል በግራ እግሩ ወደ ግብነት በመቀየር ነገሌ አርሲን ቀዳሚ አድርጓል። የመጀመሪያው አጋማሽም በነገሌ አርሲ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ 65ኛው ደቂቃ ላይ ኮሊንስ ኮፊ ከአለኝታ ማርቆስ የተቀበለውን ኳስ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ በግራ እግሩ ባስቆጠረው ድንቅ ግብ የነገሌ አርሲን መሪነት ወደ 2ለ0 አሳድጓል። ከደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዳዊት ካሳው በ73ኛው ደቂቃ ግብ በማስቆጠር ሸገር ከተማን ወደ ጨዋታው መልሷል። በ91ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ብሩክ በሙአዝ ጋሊ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀጥታ በቀይ ካርድ ወጥቶ ጨዋታውም በሰጎኖቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀላባ ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና
በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ቀን 10:00 ሰዓት ላይ በተደረገው ሌላኛው የዕለቱ ጨዋታ ሀላባ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2ለ1 በማሸነፍ ዳግም ወደ ድል ተመልሷል። በ20ኛው ደቂቃ ናትናኤል ሰለሞን ከግራ መስመር የመታውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ሀላባ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል። የመጀመሪያው አጋማሽም በሀላባ ከተማ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እንደተጀመረ በ46ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግምባሩ በማስቆጠር የሀላባ ከተማን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድቢያደርጉም በ57ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ አብዱልከሪም ራህመቱ ኳሱን በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ደስታ ወሚሾ ወደ ግብነት በመቀየር ሀድያ ሆሳዕናን ወደ ጨዋታው መልሷል።
በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነብሮቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ ጨዋታው በሀላባ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

