ሪፖርት | ተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ 2 አቻ ተጠናቋል

ሪፖርት | ተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ 2 አቻ ተጠናቋል

በአምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በባሕር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከባሕር ዳር ከተማ ጋር 2ለ2 ሲለያይ፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር 0ለ0 ተለያይተዋል።

በዐቢዩ አረጋሽ

ፋሲል ከነማ 2–2 ባህር ዳር ከተማ

በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች የታጀበው ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ የደጋፊዎችን ልዩ ድባብ ያሳየ ነበር።

ጨዋታው ተጀምሮ በ9ኛው ደቂቃ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ጄሮም ፊሊፕ ወደ ግብነት በመቀየር ፋሲል ከነማን መሪ አድርጓል። በቀሪው የመጀመሪያ አጋማሽ ሌላ ግብ ሳይቆጠር ፋሲል 1ለ0 በሆነ ውጤት ወደ ዕረፍት ገብቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፉክክሩ ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በ79ኛው ደቂቃ ታምራት ኢያሱ የተላከለትን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር የፋሲል ከነማን መሪነት ወደ 2ለ0 አሳድጎታል።

ሆኖም ባህር ዳር ከተማ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደ ጨዋታው ተመልሷል። በ83ኛው ደቂቃ መሳይ አገኘው ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት በመቀየር የጎል ልዩነቱን አጥብቦታል።

የጨዋታው ድራማ ግን በዚህ አላበቃም። በጭማሪ ደቂቃ 90+3 ላይ መሳይ አገኘው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አንተነህ ተፈራ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮታል። በዚህም ባህር ዳር ከተማ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ከመመራት ተነስቶ 2ለ2 አቻ መውጣት ችሏል።

በሌላ በኩል በጨዋታው 23ኛው ደቂቃ ላይ ከሁለት ዓመታት በፊት ሕይወቱ ያለፈው የቀድሞ የባህር ዳር ከተማ ተጫዋች አለልኝ አዘነ በክብር ታስቦ ውሏል። ደጋፊዎችና የስፖርቱ ቤተሰብ ተጫዋቹ ይለብስ የነበረውን 23 ቁጥር በመነሻ በማድረግ በደቂቃው ላይ ያሳዩት የመታሰቢያ ድባብ የጨዋታው ሌላው ልዩ ክስተት ነበር።

ኢትዮጵያ ቡና 0–0 አዳማ ከተማ

በአዲስ ከበባ ስታዲየም ቀን በተመሳሳይ 9 ሰዓት ላይ የተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ሆኖም ጥረቱን ወደ ግብነት መቀየር አልቻለም። አዳማ ከተማም ወደ ቡና የግብ ክልል ቢደርስም ግልጽ ሙከራዎችን ማድረግ ተቸግሯል።

በሁለተኛው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች የጨዋታውን ውጤት ለመቀየር ቢጥሩም የተፈለገውን ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ 90 ደቂቃዎችን አጠናቀዋል።