ጋቦን 2017፡ ቆይታ ከአፍሪካ እግርኳስ ተንታኝ ኦልዋዳ ሎትፊ ጋር

የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በጋቦን ርዕሰ መዲና ሊበርቪል ይጀምራል፡፡ 

በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምክንያቱ ያልበረደ የፓለቲካ ቀውስ በሚታይባት ጋቦት የተቋዋሚው መሪ ጂያን ፒንግ ህዝቡ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተቃውሞውን እንዲያሰማ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ የጊኒ ቢሳው፣ ዚምባቡዌ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ ተጫዋቾች በቦነስ ክፍያ ዙሪያ የከረረ ግጭትን ከሃገራቱ የእግርኳስ ፌድሬሽኖች ጋር ሲያደርጉ ነበር፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው በነዚህ ውዝግቦች ታጅቦ ዛሬ ይጀምራል፡፡ 

መቀመጫውን በፈረንሳይ ያደረገው ቱኒዚያዊው ጋዜጠኛ ኦልዋዳ ሎትፊ ስለአፍሪካ ዋንጫው የሚሰማውን ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሎትፊ የአፍሪካ እግርኳስ ላይ የሚሰራ ጋዜጠኛ ሲሆን በ2016 የግሎ ካፍ ሽልማት ላይ የሚዲያ ኤክስፐርቶች ፓናል አባል በመሆን አገልግሏል፡፡ 

ስለምድቦቹ

ሁሉም ምድቦች ጠንካራ ናቸው የተወሰኑ ሃገራት በወረቀት ላይ ደካማ ቢመስሉም፡፡ ከዚህ በፊት ላይ እንደነበሩት የአፍሪካ ዋንጫዎች ሶስት ሃገራት ብቻ አይደሉም ለዋንጫ የተገመቱት፡፡ የተወሰኑ ሃገራት ከሌሎች በጣም የተሻሉ ሆነው የሚሰማህ ስሜት በአሁኑ ውድድር ላይ የለም፡፡

የኮትዲቯር ዳግም ዋንጫውን የማንሳት እድል

ዕድሉ ከፍተኛ ነው ካላቸው ብቃት አንፃር፡፡ ቢሆንም በሜዳ ውስጥ እና በተቀያሪ ወንበር ላይ ቡድኑን ሊመራ የሚችል ተጫዋች የላቸውም፡፡ በመሃል ሜዳ ላይ ፈጣሪ የሆኑ አማካዮችን አለመያዛቸውም ይጎዳቸዋል፡፡

የጋቦን 2017 ከሌሎቹ ቀደምት የአፍሪካ ዋንጫዎች በምን ይለያል

ዋናው ልዩነት እኔ እንደማስበው ከዚህ ቀደም በነበረው ውድድር ላይ የተወሰኑ ሃገራት ከቀሪዎቹ በጣም የሰፋ ልዩነት ይታይባቸው ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ እምብዛም ነው፡፡ ከረጅም ግዜ በኃላ ተመጣጣኝ የሆነ እና ክፍት እግርኳስ የምናይበት የአፍሪካ ዋንጫ ይሆናል ብዬ አስባለው፡፡

መታየት ያለባቸው ተጫዋቾች

የአትላንታ በርጋሞ ኮትዲቯራዊው አማካይ ፍራንክ ኪሲ፣ የዩጋንዳው ፋሩክ ሚያ፣ ግብፃዊያኑ ረመዳን ሶብሂ እና መሃሙድ ካራባ፣ የማሊው ግብ ጠባቂ ጂጉኢ ዲያራ እና ዲ.ሪ. ኮንጎው አጥቂ ጆናታን ቦሊንጊ የመጫወት እድል ካገኙ ልንምለከታቸው የሚገቡ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የሰሜን አፍሪካ ቡድን የቻምፒዮንነት ዕድል

እኔ እንደማስበው አልጄሪያ እና ግብፅ ከሰባት ዓመት ድርቅ በኃላ ዋንጫው ወደ ሰሜን አፍሪካ የመመለስ የተሻለ ዕድል አላቸው፡፡ በተለይ ግብፅ ከምድባቸው ማለፍ ከቻሉ የተሻለ ርቀት መጓዝ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

ሊያስገርመን የሚችል ቡድን

እኔ ጋቦንን እመርጣለው፡፡ ጥሩ ቡድን አላቸው፡፡ አሰልጣኙም ጥሩ ነው ምንም እንኳን ከፌድሬሽኑ ጋር ቅራኔ አለው ቢባልም፡፡ ጥሩ ምድብ ውስጥ በንፅፅር ስለሚገኙ የተሻለ ርቀት ሊጓዙ ይችላሉ፡፡

የከዋክብት ተጫዋቾች የአፍሪካ ዋንጫው ላይ አለመገኘት

ከዋክብቶች ስለሌሉ ጥሩ እግርኳስ አናይም የሚል ሃሳብ ላይ ፈፅሞ አልስማማም፡፡ ጥሩ እና መልካ የሆነ ውድድር ከዋክብቶቹም ሳይኖሩ የሚኖር ይመስለኛል፡፡ ሁሌም የሚቀሩት ሰዎች ከተሳሳቱት መካከል ናቸው ብዬ አስባለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *