ፌዴሬሽኑ ወልድያ ላይ የጣለውን እገዳ በጊዜያዊነት አነሳ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በወልድያ ስፖርት ክለብ ላይ ያስተላለፈው የወድድር እገዳ ውሳኔን በጊዜያዊነት ማንሳቱን ክለቡ አስታውቋል፡፡

ወልድያ አምና በከፍተኛ ሊጉ ሲሳተፍ የክለቡ ተጫዋቾች የነበሩት ሲሳይ አማረ ፣ እዮብ ገብረአረጋዊ እና ድንበሩ መርጊያ ከክለቡ ጋር ኮንትራት እያላቸው በመሰናበታቸው በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ተጫዋቾቹ ለፌዴሬሽኑ ቅሬታቸውን አቅርበው ነበር።

ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደጉ ለቡድኑ አባላት የተሰጠውን የሽልማት ገንዘብ ለመክፈል እና የ3 ወር ደሞዝ በካሳ መልክ ለመስጠት ከአንዱ ተጫዋች በቀር የተስማማ ቢሆንም ባጋጠመው የፋይናንስ ችግር ክፍያውን መፈፀም እንዳልቻለ ከክለቡ ቡድን መሪ ሰለሞን አነጋግረኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህን ተከትሎም ወልዲያ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ ተላልፎበት እንደነበር ትላንት ማስነበባችን ይታወሳል።

አቶ ሰለሞን አነጋግረኝ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ ክለቡ ከላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ በተጫዋቾቹ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በማስገባት የክፍያ ማረጋገጫ ወረቀቱን ለፌዴሬሽኑ አስገብቶ ነበር። ነገርግን ተጫዋቾቹ የ1 ዓመት ደሞዝ በካሳ መልክ እንዲከፈላቸው በመፈለጋቸው ከክለቡ ጋር መስማማት አልቻሉም። ፌዴሬሽኑም ክለቡ እና ተጫዋቾቹ ልዩነታቸውን በማጥበብ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በማሳሰብ እገዳውን የፕሪምየር ሊጉ 1ኛ ዙር እስከሚጠናቀቅበት ጥር 29 ድረስ በጊዜያዊነት አንስቷል።

በዚህም መሰረት ወልዲያ በሊጉ 12ኛ ሳምንት በሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2009 በመርሃ ግብሩ መሰረት የሚደረግ ይሆናል።



በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልጠቀስን በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን ለራስዎ ፕሮግራም /ፅሁፍ ሲጠቀሙ ምንጭ ጠቅሰው ይጠቀሙ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *