​የጨዋታ ሪፖርት | ደደቢት የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል ፋሲል ላይ አስመዘገበ

በኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛው ሳምንት ጨዋታ ዛሬ ጎንደር አፄ ፋሲል ስታድየም ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ በሜዳውና በደጋፊው ፊት በደደቢት 1-0 ተረትቷል፡፡

በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች በታደመመበት ጨዋታ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ ፣ የአፄዎቹ ትርጉም አልባ የማጥቃት እንቅስቃሴ ፤ የደደቢት ጠንካራ የመከላከል ብቃት ታይቶበት በእንግዳው ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባበል ከተጨዋቾቹ ጋር ከተዋወቁ በኋላ ለህዝቡ በስፓርታዊ ጨዋነት ጨዋታውን እንዲከታተል መልዕክት አስተላልፈው የክለቡን ህብረ ዝማሬ በማዘመር ደጋፊውን ሲያነቃቁ መመልከት ከጨዋታው በፊት የነበረ አስገራሚ ትይንት ነበር ።

በመጀመርያው አጋማሽ ባለ ሜዳዎቹ ፋሲሎች በፈጣን እንቅስቃሴ ኳሱን በመቆጣጠር በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የጎል ክልል ለመግባት ጥረት ቢያደርጉም የተሳካ ጠንካራ የጎል እድል መፍጠር የቻሉት በ11ኛው ደቂቃ በኤርሚያስ ኃይሉ እና በ40ኛው ደቂቃ ላይ አብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት ብቻ ነው፡፡  ከዛ ውጪ አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በረጃጅም ኳስ ወደ ጎል ለመድረስ ቢሞክሩም የተደራጀውን የደደቢት የመከላከል ብቃትን ሰብረው መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በአንፃሩ እንግዶቹ ደደቢቶች 36ኛው እና 42ኛው ደቂቃ ላይ በሽመክት ጉግሳ እና በአቤል አያሌው አማካኝነት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡  የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ምንም ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተመሳሳይ የሆነ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ወደ ጎል ለመቅረብ ከሚደረግ ጥረት ይልቅ በተጨዋቾች ቅያሪና ተጨዋቾች በሚሰሩት ጥፋት ምክንያት የሚሰጡ የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተደጋግመው ታይተዋል፡፡

አፄዎቹ በአጫጭር ኳስ ወደ ጎል ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት የደደቢት አማካዮችና ተከላካዮች ቶሎ በማፈን ኳሱን በመንጠቅ በመልሶ ማጥቃት ያደርጉት የነበረው ጥረት በ86ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር ወደ መሀል ሜዳ ሰብሮ በመግባት የፋሲል ተከላካዮችን ጌታነህ ከበደን ለመቆጣጠር ሲሳቡ ተነጥሎ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሽመክት ጉግሳ በግሩም ሁኔታ ኳሷን ወደ ጎልነት በመቀየር ደደቢት አሸናፊ የሆነበትን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል ።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ በቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ለማግኘት ቢሞክሩም የተደራጀውን የደደቢት የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾችን ሰብሮ መግባት ተስኗቸው ጨዋታው በደደቢት 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎም ለደደቢት ከሜዳው ውጭ ያስመዘገበው የመጀመርያ ሦስት ነጥብ ሆኖ ሲመዘገብ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ላይ ለመቀመጥም ችሏል።

ከጨዋታው በኋላ የፋሲል ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በሰሩት ስህተት እንደተሸነፉ ተናግረዋል፡፡ ” ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ በሚገባ ኳሱን ተቆጣጥረን ተጫውተናል፡፡ አንድ ስህተት ሰርተን በመልሶ ማጥቃት ምክንያት ሶስት ነጥብ ለማግኘት ሄደን ሶስት ነጥብ አጥተናል፡፡” ብለዋል፡፡

የደደቢቱ አስራት ኃይሌ በበኩላቸው አጨዋወታቸው ለድል እንዳበቃቸው ገልጸዋል፡፡ ” ጨዋታው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ገምተን ነው የመጣነው፡፡ ምክንያቱም ከጥሩ ቡድንና ከበርካታ ደጋፊ ጋር እንደምንጫወት አውቀናል፡፡ ለዛም ነው መከላከልን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይዘን የገባነው ፤ በመልሶ ማጥቀት በፈጠርነው አጋጣሚም ሶስት ነጥብ ይዘን ወጥተናል፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *