የፊፋው አዲስ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ በአጭር ጊዜ የጉብኝት ቆይታቸውም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በደቡብ ሱዳን ጀምረዋል ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት በኢትዮጵያ እንደሚጀምሩ ቢጠበቅም በአሁኑ ሰአት በደቡብ ሱዳን እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት አፍሪካ በስምምነት ለባህሬናዊው ሼክ ሰልማን ድምጽ ቢሰጡም ደቡብ ሱዳን ከብዙሃኑ በተቃራኒ ቆማ ለጂያኒ ኢንፋንቲኖ ድምጽ ሰጥታለች፡፡ በዚህም ምክንያት በ2012 የፊፋ አባል ሀገር ከሆነችው ሀገር ጋር ወዳጅነታቸውን ያጠነከሩት ኢንፋንቲኖ ሀገሪቱን ዛሬ በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ኢንፋንቲኖ በጁባ ቆይታቸው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ደቡብ ሱዳን ከ ቤኒን የሚያደርጉትን ጨዋታ ታድመው ምሽት 2፡30 ላይ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡
ጉብኝቶች
ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከጁባ ተነስተው ምሽት 2፡30 አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን በሸራተን አዲስ ያርፋሉ፡፡ በዚሁ ምሽት ወደ ብሄራዊ ቤተመንግስት በማምራትም ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ፡፡ ነገ ጠዋት ደግሞ የአፍሪካ ህብረትን የሚጎበኙ ሲሆን በመቀጠል የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን እንዲበኙ እቅድ ተይዟል፡፡ ካዛንችስ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤትም የጉብኝታቸው አካል ነው፡፡
ፅህፈት ቤቱን እንዲጎበኙ ለምን አስፈለገ?
ኢንፋንቲኖ በነገው የፅህፈት ቤት ጉብኝታቸው የፈዴሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ሲሆን በሃገሪቱ የሊግ አወቃቀር ፣ የማርኬቲንግ እንቅስቃሴ ፣ የስፖርት መሰረተ ልማት እና የታዳጊዎች ልማት ላይ ከፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ እግርኳስን ለማጠናከር ላቀዳቸው ስራዎች ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግ የተለያዩ ፕሮፓዛሎችም ይቀርባሉ፡፡
አዲሱ የፊፋ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤትን እንዲጎበኙ እቅድ የተያዘው ፊዴሬሽኑ ሊያስገነባ ላቀደው ህንፃ ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግ ፕሬዝዳንቱን ለማሳመን እንደሆነ ከፌዴሬሽኑ አካባቢ ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴውን በተታተነ መልኩ በማድረግ ላይ ከመሆኑ ባሻገር አሁን የሚጠቀምበትን ፅህፈት ቤት የኪራይ በመሆኑ በአንድ ማእከል በመሰብሰብ ስራዎችን ለመስራት በማሰብ ህንፃ ለማስገንባት ፕሮፖዛል እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡ በነገው ጉብኝትም ፌዴሬሽኑ ፕሮፖዛሉን በባለሙያዎች አማካኝነት ለፕሬዝዳንቱ እንደሚያብራሩ ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ለኢትዮጵያ እግርኳስ መልካም ነገሮች ይዞ እንደሚመጣ ፌዴሬሽኑ ትልቅ ተስፋን ሰንቋል፡፡ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ነገ 10፡30ገደማ በመጨረስ የስራ ጉብኝት ለማድረግ እቅድ ወደያዙባቸው ሌሎች ሃገራት ጉዟቸውን ያደርጋሉ፡፡