አዲሱ የአዳማ ፈርጥ ስለ እግርኳስ ህይወቱ ይናገራል…

ዘንድሮ በተለይም ደግሞ በቅርብ በተደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ደምቆ የወጣው እና ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ውስጥ የተካተተው ወጣቱ የአዳማ ከተማ አጥቂ ዮሴፍ ታረቀኝ የዛሬ እንግዳችን ነው።

ትውልድ እና ዕድገቱ መቂ ከተማ ነው። ከልጅነቱ አንስቶ ለእግርኳስ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት በሰፈር ውስጥ መጫወት የጀመረው ይህ ተስፈኛ ወጣት በ2012 በመቶዎች ከሚቆጠሩ ታዳጊዎች መሐል ተፈትኖ የአዳማ ከተማን ከ17 ዓመት በታች ቡድንን ተቀላቀለ። በ2014 በቀጥታ የአዳማ ዋና ቡድንን ቢቀላቀልም ለግማሽ የውድድር ጊዜ ቆይታ በማድረግ ወደ ተስፋ ቡድኑ ወርዶ እንዲሰራ ተደርጎ በያዝነው የወድድር ዘመን በድጋሚ ዋና ቡድኑን መቀላቀል ችሏል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በሱዳን አስተናጋጅነት በተካሄደው 20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ላይ በመሳተፍ በስሙ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ተመልሷል።

\"\"

በአዳማ ዋነው ቡድን አብዛኛውን ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ያሳለፈው ዮሴፍ በቅርብ የሊጉ ሳምንታት ላይ የማለፍ ዕድል በማግኘት በተለይ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ብዙኋኑን እያስደመሙ ካሉ ወጣቶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል። የአዳማ ቡድን ፍሬ የሆነው ዮሴፍ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ተስፈኛ አጥቂ መሆኑን አስመስክሯል። ሶከር ኢትዮጵያም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህ ወጣት ተጫዋች የወደፊቱ ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ መሆኑ ደጋግማ እንደገለፀችው ሁሉ ዛሬም አጠቃላይ የእግርኳስ ህይወቱን ጉዞ አስመልክታ ከዮሴፍ ታረቀኝ ጋር ያደረገችውን እንዲህ አሰናድታ አቅርባዋለች።

ወደ እግር ኳስ የገባህበት አጋጣሚ እንዴት ነበር ?

\”እግርኳስን የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ከሰፈር ልጆች ጋር በጨርቅ ኳስ ነው። አባቴም የተሻለ ኳስ እየገዛልኝ የተጫወትኩባቸው ግዜያት ነበሩ። በሰፈርም በትምህርት ቤት ደረጃም ተጫውቻለሁ። በዚህ መሀል ብዙ አሰልጣኞች አሰልጥነውኛል በክለብ ደረጃ ግን ወደ አዳማ ከሄድኩ በኋላ ነው መጫወት የጀመርኩት።\”

\"\"

ወደ አዳማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን እንዴት ተቀላቀልክ ?

\”ክረምት ላይ ሁሌም የሙከራ ጊዜ ይሰጥ ነበር ፤ ምክንያቱም ሰፈር ላይ በየቀበሌው በየሰፈሩ ያሉ ወጣቶች የት መድረስ እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ነገ የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ የሙከራ ጊዜ ይሰጣሉ።
በዚህ ዕድል እኔ ተጠቃሚ ሆኜ አስራ አንደኛ ክፍልን አልፌ አስራ ሁለተኛ መግቢያ ላይ ከ300-400 ታዳጊ ሲመለመል ከነሱ ውስጥ አንዱ እኔ ሆኜ የሙከራ ዕድሉ ተጠቃሚ ሆኛለሁ።\”

ከመቂ ወደ አዳማ የሄድከው ለዚሁ ሙከራ ነበር ?

\”በ2010 ለትምህርት ነው አዳማ የሄድኩት። አስራ አንደኛ  ክፍልን እየተማርኩ የሱፍ ናስር የሚባል አሰልጣኝ ጋር የቀበሌ ቡድን ውስጥ ገብቼ  8 ወር ገደማ ከሰራሁ በኋላ ክረምት ላይ አዳማ ተስፋ ገባሁ። ወደ አዳማ አመጣጤ ግን ለትምህርትም ለእግርኳስም ነበር። አዲስ አበባ የመሄድ ዕድሉም ነበረኝ። እዛ ግን የኑሮ ውድነት አለ ስለሚባል በአዳማ ከተማ ከመማር ጎን ለጎን ኳሱንም የጀመርኩት። አዳማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን 2012 የተቀላቀልኩ ቢሆንም በወቅቱ ግን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ውድድር ባለመደረጉ የጀመርኩት በ2013 ነበር።\”

\"\"

በአዳማ ከ17 ዓመት በታች ቆይታህ ምን ይመስል ነበር ?

\”ብዙ ፈተናዎች ነበሩብኝ። ለምግብና ለቤት ኪራይ ወጪ ራሱ ከክለቡ ሳይሆን አሰልጣኞቼና ከቤተሰብ በሚደረግልኝ ድጋፍ ነበር የምረዳው። ወደ ውድድር ስገባም በራስ መተማመኔ ከፍተኛ ነበር። ከአራት መቶ ልጆች እኔ የተመረጥኩት አቅም ስላለኝ ነው ብዬ ራሴን አሳምኜ በሰውነቴ ሳይሆን በአዕምሮዬ ስለምጫወት የተሻለ ነገር በማሳየት የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች መሆን ችያለሁ።\”

ከአዳማ 17 ዓመት በታች ወደ 20 ዓመት በታች መቼ አደክ ?

\”ከ17 ዓመት በታች ጥሩ ጊዜን ካሳለፍኩ በኋላ ሐምሌ 2013 ቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን ነው ያደግኩት። 2014 የውድድር ዓመትን ከአዳማ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝና ምክትል አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ስር ግማሽ የውድድር ዓመትን በዋና ቡድን አሳልፌ ግማሹን የውድድር ዓመት ግን ወደ 20 ዓመት በታች ቡድኑ ወርጄ ጨርሻለሁ።\”

ከ20 ዓመት ቡድኑ ጋር የነበረህ ቆይታ ምን ይመስል ነበር ?

\”እሱም ከባድ ነበር። ምክንያቱም ከዋናው ቡድን ወርጄ ወደዚያ ስለሄድኩ የሥነ-ልቦና ጉዳት አለው። በጉዳት ከሜዳ ርቄም ስለነበር ወደ ጨዋታ ስመለስ የአቋም መውረድ ገጥሞኝም ነበር። በዛ አሰልጣኞችም የቡድን ጓደኞችም ደስተኛ አይሆኑም እና በዚህ በጣም ከባድ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት ግን ከፈጣሪ ጋር አልፌዋለሁ።\”

\"\"

በዚህ ዓመት ነውና ወደ ዋናው ቡድን ያደከው የዋናው ቡድን ጅማሬህን እንዴት ትገልፀዋለህ ?

\”ባህር ዳር ላይ ቡድናችን አሪፍ ነበር ፤ ድሬዳዋ ከመጣን በኋላ ነው መቀዛቀዝ የታየው። ከብሔራዊ ቡድን መልስ ድሬዳዋ ሦስት ጨዋታ ካደረጉ በኋላ ነው የተቀላቀልኩት ከዛ በኋላ ተቀይሮ የመግባት ዕድሎች አግኝቻለው። ቡድናችንም ወደ ማሸነፍ መንገድ መጣ ፤ በተለይ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ጥሩ ነበርን። በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ነው ነጥብ የጣልነው። በአጠቃላይ ግን ያየሁት ነገር ጥሩ ነው። በግልም ጥሩ መጫወት እንደምችል በልምምድ ሜዳ ላይ አሳይቻለው ፤ ከዛ ድጋሜ ወደ ድሬዳዋ ከተመለስን በኋላ ነው ወደ ቋሚ አሰላለፍ መግባት የቻልኩት። ችግሮች ሲፈጠሩ በምክንያት ነው። እነሱ ከተፈጠረው ችግር በኋላ ከቡድኑ ራቁ እኛም ያንን ዕድል ሲሰጠን በአግባቡ ተጠቀምን። ሁሉም ነገር የፈጣሪ ሥራ ነው ፤ እኔ በዚህ ፍጥነት ወደ ቋሚ አሰላለፍ እገባለው ብዬ አስቤ አላቅውም። አሁን ያለውን ብቃት ለማስቀጠል ደግሞ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው።\”

\"\"

በዋናው ቡድን ያደረከው የመጀመሪያ ጨዋታ እንዴት ነበር ?

\”የመጀመርያ ጨዋታዬ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነበር። ደቂቃውም ሀያ አምስት ደቂቃ ያህል ነው የተጫወትኩት። እንድያውም ከሌሎች ከተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች የመጀመርያው በጣም ቀሎኝ ነበር። ምክንያቱም ደግሞ በመጀመርያው ጨዋታዬ ተጋጣምያችን አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቶባቸው በሙሉ አቅማችን ያጠቃንበት ጨዋታ ስለነበር ነው።\”

የሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በደቡብ ሱዳን ተሸንፎ ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ የሆነው የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባል ነበርክ። ብዙዎች ቡድኑ ለፍፃሜ ያለማለፉ ተጠያቂ ያደርጉሀል ፤ ምን ምላሽ አለህ ?

\”በመጨረሻው ደቂቃ አካባቢ ማስቆጠር የነበረብን ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል ዕድል አግኝቼ ነበር። ከኔ በተሻለ ቦታ ለነበረው ቡድን አጋሬ መስጠት ስችል የእነርሱ ተከላካይ ታክል ወርዶ ጨርፎብኝ የጎል አጋጣሚው መክኗል። አንዳንዴ ተጫዋች እስከሆንክ ድረስ ሜዳ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠራል። ፍፁም ቅጣት ምትም ልሰት እችላለው አይደለም በእንቅስቃሴ ውስጥ ያለ ኳስን፣ ግን ከዛ በፊት ጎሎችን አግብቼ እንደነበረ መረሳት የለበትም። እንዲህ ያለ ነገር አይፈጠርም ከተባል ስህተቱን እቀበላለው።\”

\"\"

በውድድሩ ጎል አግብተህ ልታሳይ ስለነበረው ነገርስ ምን ትላለህ ?

\”ይሄ የግል ጉዳዬ ነው። የፖለቲካም ይዘት አልነበረውም። የኔ ማስታወሻ ሰው የሰጠኝ ነበር። ይህን ወረቀት ለልጁ ማስታወሻ ለማሳየት ነበር አልተሳካም። ፓለቲካዊ ነገር መስሎት ነጠቀኝ።\”

ማነው የነጠቀህ ? ፁሁፉስ ምን ዓይነት መልዕክት እንደነበረው ማወቅ ይቻላል ?

\”የነጠቀኝ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወንድም እንዳለኢየሱስ ነው። አሁንም ወረቀቱ ወስዶት እርሱ ጋር ነው ያለው። በጊዜው ወረቀቱን ለምክትል ለአሰልጣኝ አፈወርቅ ያዝልኝ እና ጎል ሳገባ መጥቼ እቀበልሀለው ብዬ ሰጥቸው ነበር። ካዛ ጎሉን አግብቼ ተቀብዬ ላሳይ ስል ነው የነጠቀኝ። የሚገርመው ምን እንደተፃፈት ምን እንደሚል ሳያቅ ነው የነጠቀኝ። ፅሁፉ \”እኔ ብቻ ” የሚል ነበር።

\"\"

\’በራስ መተማመኑ አንዳንዴ ከልክ በላይ ነው\’ በሚል ትችት ሲቀርብብህ ይሰማል ምን ምላሽ አለህ ?

\”ሜዳ ውስጥ በማደርጋቸው ነገሮች ይህ ነገር ያለብኝ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። ያው ነኝም ብዬ አስባለው ባህሪዬ ስለሆነ በራስህ ካልተማመንክ እግርኳስ ላይ ከባድ ነው። ሜዳ ውስጥ በራስህ የማትተማመን ከሆነ ኃላፊነቶችን ለመውሰድ ትቸገራለህ። ስለዚህ የሚባለው ነገር በተወሰነ መልኩ ልክ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ አልቀበለውም። እስከ ዛሬ አዋጥቶኝ ነው እዚህ የደረስኩት ። በራስ መተማመኔ እንደዚህ ባይሆን እዚህ ቦታ ላይም ከፈጣሪ ጋር አልደርስም ነበር። ስለዚህ ከልክ ያለፈ ነው የሚለውን አልስማማም።\”

\"\"

አሁን ደግሞ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ተመርጠሀል ፤ ምን ስሜት ፈጠረብህ ?

\”ምርጫው አልጠበቅኩት ነው። ማለት በዚህ ፍጥነት የሀገሬን ማልያ እለብሳለው የሚል ግምት አልነበረኝም። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግን አሁን ባሳካሁት ነገር አልኩራራም። ገና ብዙ ነገር እንደሚጠብቀኝ ነው የማስበው ፤ ፈጣሪ ብሎት ከጉዳት ነፃ ከሆንኩ ጥሩ ደረጃ ለመድረስ ነው በመስራት የምገኘው። እዚህ ደረጃ ለመድረሴ በህይወቴ ውስጥ ብዙ ሰው አስተዋፅዖ አድርጓል ለሁላቸውም በጣም አመሰግናለው። ለቤተሰቦቼ ለአፈወርቅ ፣ ለፍቅር እና መቂ እያለው ላገዙኝ ጌታሁን ፣ ነጋ በዙርያዬ ብዙ አሰልጣኞች አሉ እነሱን በጣም ማመስገን እፈልጋለው። አሰልጣኝ ይታገሱም አምኖብኝ ዕድሉ ስለሰጠኝ ለብሔራዊ ቡድንም አሰልጣኝ ዕድሉን ስለሰጠኝ ማመስገን እፈልጋለው።\”

በቀጣይ ምን ታስባለህ ?

\”የልጅነት ህልሜን አግኝቼዋለው።
ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር የምፈልገው ሆኛለው ፤ አሁን ደግሞ ያገኘሁትን ዕድል ተጠቅሜ ለቀጣይ ትልቅ ተጫዋች ለመሆን ነው የማስበው ለሱም ጠንክሬ እየሰራው ነው። ከዛ በኋላም ከሀገር ውጭ ወጥቶ የመጫወት ህልም አለኝ።\”

\"\"

በዚህ ጉዞህ ውስጥ የቤተሰቦችህ አስተዋፅዖ እንዴት ነበር ?

\”ቤተሰቦቼ በጣም ይደግፉኛል። ስታድየም ድረስ መጥተው ጨዋታዬን ያያሉ። ካለ ቤተሰቤ ጥረት እዚህ ደረጃ መድረስ አይታሰብም ነበር ፤ በጣም ደግፈውኛል በጥሩም በመጥፎም ግዜ ከጎኔ ነበሩ። በዚህ አጋጣሚ እናት እና አባቴን ከልብ አመሰግናለው።\”

በመጨረሻ አንተ በነበርክበት ደረጃ ለሚገኙ ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾች ምታስተላልፈው መልዕክት አለህ ?

\”ዋናው መሰረታዊ ነገር ጠንክሮ መስራት ነው። ሌላው ከአሰልጣኝ እና ከቤተሰብ ፍቃድ ውጪ ምንም ዓይነት ነገር አለማድረግ። ጠንክሮ መስራት እና ተስፋ አለመቁረጥ ወሳኝ ነገሮች ናቸው።\”