ባህርዳር ከተማ በመርሐ-ግብር ሽግሽጉ ዙሪያ ቅሬታ አሰምቷል

ባህርዳር ከተማ በመርሐ-ግብር ሽግሽጉ ዙሪያ ቅሬታ አሰምቷል

ዛሬ ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሚጫወተው ባህር ዳር ከተማ አግባብ በሌለው ምክንያት ጨዋታው እንዲራዘም ተደርጓል በሚል ቅሬታ በማስገባት ጨዋታውን ዛሬ እንዲያከናውን ጥያቄ አስገብቷል።

ዛሬ እንዲደረጉ መርሐ-ግብር ተይዞላቸው የነበሩት የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሀዋሳ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የሰዓት እና የሜዳ ለውጥ እንደተደረገባቸው የሊጉ የበላይ አካል መግለፁ አይዘነጋም። እርግጥ የወላይታ ድቻ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ የሜዳ ለውጥ ብቻ ተደርጎበት በተያዘለት መርሐ-ግብር መሰረት ዛሬ ሲደረግ የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ግን ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። ይህንንም ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ የቅሬታ ደብዳቤ ለአክሲዮን ማኅበሩ ማስገባቱን ለዝግጅት ክፍላችን የላከልን መረጃ ያመላክታል።

ባህር ዳር ከተማ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው ደብዳቤ “የውድድር ደንቡ ማንኛውም ክለብ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ በሚያወጣው ፕሮግራም እና ቦታ የመጫወት ግዴታ እንዳለበት እየገለፀ አሁን ግን አንድን ክለብ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የውድድር ቦታው ሀዋሳ ከተማ ላይ ሆኖ እያለ ከአዲስ አበባ እየተመላለሰ ስለሚጫወት የሚል ምክንያት መስጠት ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ክለባችን ያምናል” ብሏል።

ክለቡ አያይዞም ነገ ለመጫወት ፕሮግራም እንደተያዘላቸው ክለቦች እንደተደረገው የጨዋታ ሽግሽግ ሁሉ ለእነሱም “ሚዛናዊ” የሆነ የፕሮግራም ለውጥ እንዲደረግና በተለወጠው ፕሮግራም መሰረት 10 ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ እንዲጫወቱ እንዲደረግ ጠይቀዋል።