ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

የ29ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ በታሪካቸው ለ46 ጊዜ በሚያደርጉት ጨዋታ አሀዱ ይላል።

ከስምንት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኃላ ሦስት  ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው መንገዳቸውን ያቃኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአርባ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ነጥባቸውን አርባ ቤት ካስገቡ ስድስት የሊጉ ክለቦች ውስጥ የሚጠቀሱት ፈረሰኞቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወይም በሰንጠረዡ ወገብ ይበልጥ ለመደላደል አሁንም ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል። ቡድኑ ብዙ ድክመቶች ከተስተዋሉበት የሳምንታት ጉዞ ተላቆ ወደ ጥሩ ብቃት በመምጣት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገቡ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ሽቅብ ለመውጣትም ሆነ ለማሽቆልቆል አማካይ ካለው ደረጃው ተሻግሮ በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ለመደላደል የወጥነት ችግሩን ጨርሶ መፍታት ግድ ይለዋል። በተለይም አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያሉ እዚህ የደረሱት የፊት እና የኋላ ክፍል ጥምረቶቹ በጥሩ ብቃት በወጥነት መዝለቅ ይኖርባቸዋል። በተለይም ድል አልባ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ሁለት ግቦች ብቻ አስቆጥሮ በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐ-ግብሮች አምስት ግቦች በማስቆጠር መሻሻል ያሳየው የፊት መስመሩ ከዚህም በላይ መሻሻል ይጠበቅበታል።

በሀያ ሦስት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ያላቸውን የስድስት ነጥቦች ልዩነት ለማጥበብ ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ።

ድል ካደረጉት ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው አዳማ ከተማዎች ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ቢያጠናቅቁም ያሳዩት ውስን መሻሻል ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በቂ አልሆነላቸውም። ቡድኑ በሊጉ ግርጌ የተቀመጠውን ወልዋሎ እና የቅርብ ተፎካካሪው መቐለ በገጠመባቸውና በአንፃራዊነት ቀለል ያሉ ተጋጣሚዎች ባገኘባቸው ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማሳካት ባለመቻሉ ከወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ያለው የነጥብ ልዩነት በስድስት ረግቷል። ቡድኑ በቀጠናው ዙርያ ያሉ ክለቦች እያሳዩት ካለው ብቃት አንፃር ከወራጅነት ስጋቱ ለመላቀቅ ያለው ዕድል ጠባብ አይደለም፤ ሆኖም ጉዞው በድል ለማጀብ በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ የነበረው አባካኝነት ማረም መቻል አለበት። ከዚህ በተጨማሪም ተጋጣሚው በማጥቃቱ ረገድ ውስን መሻሻል እያሳየ የዘለቀ እንደመሆኑ በሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ካስተናገደ በኋላ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ጥቃቶች በመመከት ረገድ ጥሩ የተንቀሳቀሰውን የኋላ ክፍሉ ጥንካሬ በነገው ዕለት ማስቀጠል ግድ ይለዋል።

በዚህ የጨዋታ ሳምንት 14ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ እርሰበርስ የሚገናኙ መሆናቸውም በዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ለአዳማ ከተማ ያለው ትርጉም ላቅ ያለ ነው።

በፈረሰኞቹ በኩል ባለፈው ሳምንት በቅጣት ምክንያት ያልነበረውን አጥቂውን ቢንያም ፍቅሩ ቅጣቱን በመጨረሱ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። ሌሎች የቡድኑ አባላትም ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ ሆነው የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ። በአዳማ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 45 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ 24 ጊዜ ድል ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 61 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጨዋታዎችን በድል የተወጣው አዳማ ከተማ ደግሞ 33 ግቦችን አስቆጥሯል። ክለቦቹ 13 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።