የሐዋሳ ከተማ ቆይታ መዝጊያ በነበረው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና እና ስሑል ሽረ 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ መጋራት ችለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሐዋሳ ከተማ ቆይታውን አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ተረኛ ከተማ የሚያመራበት የመጨረሻ ጨዋታ ምሽት 12:00 ሲል ሀድያ ሆሳዕናን ከ ስሑል ሽረ ጋር አገናኝቷል። ሀድያ ሆሳዕናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ድራማዊ በሆነ ትዕይንት ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻ ቀሪ 10 ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ወልዋሎ ዓ.ዩን 3-2 በሆነ ውጤት ካሸነፉበት አሰላለፍ በረከት ወንድሙ እና ብሩክ በየነን በማስወጣት በየነ ባንጃ እና ማሞ አየለን ሲያስገቡ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው ከመቻል ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ አራት ተጫዋቾችን የቀየሩ ሲሆን ክፍሎም ገ/ሂወት፣ መሐመድ ሱሌማን፣ ብሩክ ሀዱሽ እና ሄኖክ ተወልደን በማስወጣት ነፃነት ገብረመድህን፣ መሀመድ አብዱል ላጢፍ፣ ፋሲል አስማማው እና አላዛር ሽመልስ እነሱን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ጨዋታው ከጅማሬው አንስቶ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን ያስመለከተን ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ በሆነ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ስሑል ሽረዎች መሪ መሆን የሚችሉበትን ዕድል አምክነዋል። ብርሃኑ አዳሙ ይዞት የገባውን ኳስ ከፋሲል አስማማው ጋር ጥሩ በሆነ አንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በግቡ ቋሚ ወደ ውጭ ወጥቶበታል።
ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የሚችሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዓብ ግዛው ጥሩ በሆነ ምልከታ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ በሳጥኑ የቀኝ መስመር ውስጥ በመግባት ሊያቃብል መስሎ በረኛውን አታሎ ብልጠት የታከለበትን ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ አድርጓል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ስሑል ሽረዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ኳስን ተቆጣጥረው ወደፊት ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን ሀድያዎች የያዙትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ጥንቃቄን ምርጫቸው በማድረግ በቁጥር ወደኋላ በዛ ብለው በመከላከል ግባቸውን ሳያስደፍሩ የመጀመሪያውን አጋማሽ አጠናቀው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆኝ መሻሻሎችን በማሳየት የተመለሱት ስሑል ሽረዎች ወደ ኋላ ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል ስራ ላይ የተጠመዱትን የሀድያ ተከላካዮች አልፎ ግብ ለማስቆጠር የተለያዩ ዘዴዎችን ሞክረዋል። ሀሳባቸውም ተሳክቶላቸው አቻ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር ሽመልስ በግራ መስመር ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ሳጥን ይዞት በመግባት የመታውን ኳስ የሀድያው ተጫዋች ቃለአብ ውብሸት በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ስሑል ሽረዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከተቆጠረው ግብ በስተቀር ምንም አይነት ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ እና ግብ ሳያስመለክተን 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።