ነገ በአዳማ ከተማ መካሄድ የሚጀምረው የ31ኛ ሳምንት መውረዳቸው ያረጋገጡት ወልዋሎዎች እና በስድስት የጨዋታ ሳምንታት ዕድሜ ውስጥ ከዋንጫ ተፎካካሪነት ወደ ላለመውረድ የሚደረገው ፍልምያ ያሽቆለቆሉት አርባምንጭ ከተማዎች በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል።
በአስራ አራት ነጥቦች ግርጌው ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነገ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወልዋሎ በቅርብ ሳምንታት በውድድር ዓመቱ ካሳየው እጅግ የወረደ ብቃት አንፃራዊ የሜዳ ላይ መሻሻል አስመልክቶ ነበር። ሆኖም በውድድር ዓመቱ አንድ ድል ብቻ ማስመዝገቡ እንዲሁም ከሌሎች የሊጉ ክለቦች የበለጠ በአስራ ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱ በጊዜ መውረዱን እንዲያፋጥን አድርጎበታል። ቡድኑ መውረዱን አረጋግጦ ነገ ወደ ሜዳ ስለሚገባ ምናልባት ከጫና ነፃ ሆኖ ሊጫወት ስለሚችል ከወትሮ የተሻለ ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ዕድል እንዳለም ይገመታል።
በ2010 ዓ.ም ወደ ሊጉ ካደገ በኋላ በኮቪድ 19 ምክንያት እስከ ተቋረጠው የ2012 ውድድር ዓመት በመሳተፍ ላይ ቆይቶ ዘንድሮ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የወረደው ወልዋሎ ከሊጉ መሰናበቱ ባሳለፍነው ሳምንት በማወቁ ለክብር እና ለክብር ብቻ ጨዋታዎችን ያደርጋል። ሆኖም በተሻለ መንገድ የውድድር ዓመቱን ለማገባደድ ባለፉት ሳምንታት ጥሩ መሻሻል ያሳየው የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ማሳደግ ይኖርበታል።
በሰላሣ አምስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር ባስመዘገቡት ደካማ ውጤት መነሻነት ደረጃቸው እጅጉን አሽቆልቁሎ የወራጅነት ስጋት ተደቅኖባቸዋል።
ድል ካስመዘገቡ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው እንዲሁም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በመደዳ ሽንፈት ያስተናገዱት አዞዎቹ በ24ኛው ሳምንት በ2ኛ ደረጃ ላይ ከነበረው ባህርዳር ከተማ በሦስት ነጥብ ርቀው 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ነበር፤ በ24ኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ጨዋታ በኋላ በተከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ግን ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች አስራ ሰባቱን ጥለው አንዱን ብቻ ማሳካታቸውን ተከትሎ በስድስት የጨዋታ ሳምንታት ዕድሜ ላለመውረድ በሚደረገው ፍልምያ ተገኝተዋል።
ሳይታሰብ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ካሉ ክለቦች ጋር ነጥቡ እየተቀራረቡ በመሆኑ በቶሎ ከድል ጋር ተገናኝተው በአስተማማኝ የነጥብ ርቀት ላይ መቀመጥ የሚያስፈልጋቸው አዞዎቹ ከምንም ነገር በላይ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል። አሰልጣኝ በረከት ደሙ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው እና ከዚህ ቀደም ውጤታማው ቀጥተኛ አጨዋወት የነበረውን የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ከማሻሻል በተጨማሪ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን በማስተናገድ በደካማ ወቅታዊ ብቃት ላይ ያለው የተከላካይ ክፍላቸውንም ማስተካከል ይኖርባቸዋል።
በውጤትም ይሁን በእንቅስቃሴ ረገድ ሲለካ ዘንድሮ ወደ ሊጉ ከተቀላቀሉ አምስት ክለቦች የተሻለ የውድድር ዓመት ያሳለፉት አዞዎቹ በሜዳ ላይ የገጠማቸው መቀዛቀዝ ከመፍታት ባለፈ የቡድኑ ስነ-ልቦና በመጠገን ረገድ ሰፋፊ ስራዎች መስራትም ግድ ይላቸዋል።
በወልዋሎ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበቱት ቡልቻ ሹራ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ሳምሶን ጥላሁን ነገም በጉዳት ምክንያት በጨዋታው አይሳተፉም። ዳዋ ሆቴሳም በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከቡድኑ ጋር አይገኝም ሀብታሙ ንጉሴ ግን ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።በአርባምንጭ ከተማ በኩል በላይ ገዛኸኝ እና አሸናፊ ፊዳ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በ3 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ አንድ አንድ ድል ሲያስመዘግቡ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወልዋሎ 4 በአንፃሩ አርባምንጭ 3 ጎልን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።