አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታጅበው ባህርዳር ከተማን 2ለ0 በማሸነፍ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
በፌዴራል ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መጀመሪያ ፊሽካ በሞቃታማው አዳማ አየር ጅማሮውን ያደረገው የቀን ዘጠኝ ሰዓቱ የጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያው መርሐግብር አዳማ ከተማን ከባህርዳር ከተማ አገናኝቷል። አዳማ ከተማ በ32ኛው ጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 1ለ0 ሲያሸንፉ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ባህር ዳር ከተማ በበኩላቸው በ32ኛው ጨዋታ ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ 2ለ0 ሲረቱ ይዘው ከገቡት የመጀመሪያ አሰላለፋቸው የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ፔፔ ሰይዶን በአላዛር ማርቆስ ፣ወንድሜነህ ደረጄን በክንዱ ባየልኝ፣ መሳይ አገኘሁን በአቤል ማሙሽ ተክተው ገብተዋል።
ገና ጨዋታው እንደጀመረ አዳማ ከተማዎች አስቆጪ የሚባል የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ጨዋታውን ሲጀምሩ በ2ኛው ደቂቃ ሐይለሚካኤል አደፍረስ እና አድናን ረሻድ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝተው ወደ ግብ ያደረጉትን ሙከራ የጣና ሞገዶች ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው እንዴትም ተረባርበው አውጥተውባቸዋል።
ጨዋታው ለአዳማ ከተማዎች ወሳኝ ከመሆኑ አንፃር ከወራጅ ቀጠናውም ለመውጣት ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ወደፊት እየሄዱ የግብ አጋጣሚ በመፍጠር ረገድ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። ሆኖም ግን የጠራ አደገኛ የሚባል አጋጣሚ በመፍጠር ረገድ ደካማ ነበሩ። ባህርዳር ከተማዎች በበኩላቸው በመጀመሪያ አጋማሽ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ይጣሩ እንጂ ከጥረት ውጪ ጠንካራ የሚባል አጋጣሚ መፍጠር ግን አልተቻላቸውም። በዚህም በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ሆኖ የዋሉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል።
የግብ እድሎችን በመፈጠር ብልጫ የነበራቸው አዳማ ከተማዎች በ29ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ በአጫጭር ንክኪ የተገኘውን ኳስ አቤኔዘር ሲሳይ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ እንዴትም አግዶባቸዋል። የጣና ሞገዶች በአንፃራዊነት እድሎችን በመፍጠር ረገድ ደካማ እንቅሰቃሴ አስመልክተውናል፤ ሆኖም ግን34ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ናትናኤል ተፈራ ሲያግድበት ድጋሚ ያገኙትን አጋጣሚ ተከላካዮቹ እንዴትም ተረባርው ያርቁት እንጂ የጣና ሞገዶች ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።
አጋማሹም ተመጣጣኝ ፉክክር እየታየበት ቢቀጥልም አዳማ ከተማ ግብ አስቆጥረው ቀዳሚ ለመሆን በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸውን ሜዳ ክፍል ሲጎበኙ ለመመለከት ችለናል። አጋማሹም ግብ ሳይስመለከትን 0ለ0 በሆነ ወጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ ጠንከር ብለው የገቡት ባርህዳሮች በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ከመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለ የግብ ማግባት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አስተውለናል። በዚህም ፍፁም አለሙ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አከታትሎ ያደረጋቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ይቅሩ እንጂ በባርዳር ከተማዎች በኩል መነቃቃትን የፈጠሩ ሙከራዎች ነበሩ። አዳማ ከተማዎችን ጫና ማድረጋቸውን ቀጥለው 54ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ አደገኛ ሙከራ በፍቅሩ አለማየሁ አማካኝነት አድርገው አላዛር ማርቆስ አውጥቶባቸዋል።
በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደፊት በመሄድ ረገድ የኋላ ኋላ ብልጫ የወሰዱት አዳማ ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ በቢኒያም አይተን አማካኝነት አግኝተዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለው ኳስ ተጨርፎ ነቢል ኑሪ ጋር ደርሶ በግንባሩ ገጭቶ ያሻገረለትን ኳስ ቢኒያም አይተን በብልጠት ደርሶ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
የግብ ብልጫን የወሰዱት አዳማ ከተማዎች ከግቡ መቆጠር በኋላ ተረጋግተው ኳስ መስርተው በራሳቸው ሜዳ እያዘወትሩ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት ሲሄዱ አስተውለናል። ባህርዳር ከተማዎች በአንፃራዊነት ወደ ፊት ሄደው ጥቃት ባይሰነዙረም በረጃጅም ኳሶች ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ ደቂቃው ወደ 70ዎቹን ተሻግሯል።
ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሲያመራ ባህርዳር ከተማዎች የሚያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብነት ለመቀየር በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል እየደረሱ የአዳማ ከተማዎችን ተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ ሲፈትኑ መመለክት ብንችልም እድሎችን ወደ ግብነት ለመቀየር እጅግ ሲቸገሩና አጋጣሚዎቹን በቀላሉ ሲነጠቁ እንዲሁም ሲበላሽባቸው አስተውለናል። አዳማ ከተማዎች በአንፃራዊነት ወሳኙ ሶስት ነጥብ አስጠብቀው ለመውጣት ከራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው ኳሶችን በማራቅ የተጠመዱበትን የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ሲያሳልፉ ተመልክተናል።
በርከት ያለ የቆመ ኳስ ባለቀ ሰዓት ያግኙ የ የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች 87ኛው ደቂቃ ላይ በቅዱስ ዩሐንስ አማካኝነት የቆመ ኳስ ወደ ግብ ተመቶ ግብ ጠባቂው አግዶበት እራሱ ኳስ ተሻምቶ ወደ ግብነት ቀይረው አቻ ቢሆኑም የእለቱ ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ ቀድሞ ጥፋት ተሰርቷል በሚል ግቡ ተሽሮባቸዋል።
ጨዋታው በአንዱ ግብ የሚጠናቀቅ እየመሰለ መደበኛው የጨዋታ ክፍል ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው የገቡት አዳማ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 91ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በፈጣን ሽግግር ኳስ ይዘው ገብተው ቢኒያም አይነተን ኳስ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ብቻውን ሲጠባብቅ ለነበረው ሙሴ ኪሮስ ኳስ አሻግሮለት ሙሴ ኪሮስ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን አጠናክሯል። ጨዋታውም አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታጅበው ባህርዳር ከተማን በማሸነፍ በከተማቸው ቆይታ ሶስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ደረጃቸውን በማሻሻል ተቋጭቷል።