ኢትዮጵያ ቡና ከ540 ደቂቃዎች በኃላ ግብ ባስተናገዱበት ጨዋታ ባስተናገዱት ሽንፈት የዋንጫ ተስፋቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ከተዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከቀናት በፊት ባህርዳር ከተማን 2ለ0 ያሸነፈውን ቡድን በዛሬው ጨዋታ ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ከወልዋሎ ጋር ያለ ጎል አጠናቀው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ግን በሦስቱ ላይ ቅያሪን አድርገዋል። ራምኬል ጀምስን በደሳለኝ ከተማ ፣ ስንታየሁ ዋለጪን በሚኪያስ ፀጋዬ እንዲሁም አማኑኤል አድማሱን በዳዊት ሽፈራው ተክተዋቸዋል።
አዞዎቹ በሊጉ ለመክረም ነጥባቸውን ለማሳደግ ቡናማዎቹ በበኩላቸው ከመሪው ያላቸውን ነጥብ በማጥበብ በዋንጫ ፉክክር እስከ መጨረሻው ለመዝለቅ የሚረዳቸውን ውጤት ለመያዝ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያዎቹ ሰላሳ ደቂቃዎች ኳስን ከማንሸራሸር የዘለለ የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በአመዛኙ መሐል ሜዳ ከነበሩ የኳስ ንክኪዎች በቀር ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ መረጋጋቶች ያልነበሩት ጨዋታ በ9ነኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከቀኝ ረጂብ ሚፍታህ ያሻማውን የግብ ዘቡ እድሪሳ አጎጆጎ መቆጣጠር ተስኖት ከጀርባው ነፃ ሆኖ ኳሷን ያገኘው ዳዊት ሽፈራው በቀላሉ ያገኛትን ዕድል ቢመታም ዒላማማዋን መጠበቅ ሳትችል ኳሷ ወጥታለች።
አማካይ ክፍል ላይ ጥቅጥቅ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን የቀጠለው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች አዞዎቹ ወደ መስመር በተለይ ወደ ግራ በፍቅር ወዳለበት ቦታ መነሳትን መርጠው አልያም ደግሞ በሁለተኛው አማራጫቸው ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ የርቀት ሙከራዎች ቡናማዎቹ በአንፃሩ ከመስመር በጥልቀት ወደ ውስጥ ተስቦ በመጫወት በሌላ በኩል ደግሞ መሐል ለመሐል በሰንጣቂ ኳሶች አማራጭ የማጥቃት መነሻቸውን አድርገው ለመጫወት ሲጥሩ አስተውለተናል።
ጨዋታው ሰላሳዎቹን ደቂቃዎች ሲሻገር መጠነኛ የግብ ዕድሎች መፈጠር የቻሉት ሲሆን 31ኛው ደቂቃ አርባምንጮች ቡታቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም የያዘበት በቡና በኩል 33ኛው ደቂቃ ዋሳዋ ከራስ ሜዳ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ዲቫይን ወደ ሳጥን ጠለቅ ብሎ የሰጠውን ኮንኮኒ ሀፊዝ ከግቡ ከቅርብ ርቀት ሆኖ ያደረጋት ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት ተገጭታ በሚያስቆጭ መልኩ ከግብነት መክናለች። 40ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ግን አርባምንጮች ጎል አስቆጥረዋል ፣ ይሁን እንዳሻው ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ቡጣቃ ሻመና በግንባር ገጭቶ ከ540 ደቂቃዎች (ከ6 ጨዋታዎች) በኋላ ዳላንድ ኢብራሂም መረብ ላይ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
ከዕረፍት ቡናማዎቹ ዳዊት ሽፈራው እና ሚኪያስ ፀጋዬን በእስራኤል ሸጎሌ እና ሲዲ ማታላ ተክተው የተመለሱበት ነበር። ከመጀመሪያው መጠነኛ የአጀማመር መነቃቃቶች የነበሩት ሁለተኛው አጋማሽ በ47ኛው ደቂቃ አርባምንጮች አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ዳላንድ ኢብራሂም የያዘበት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቡናማዎቹ እስራኤል ሸጎሌ ከቀኝ ሳጥኑ ሆኖ ያገኘውን ኳስ ቢመታም እድሪሳ አጎጆጎ መክቶበታል። ተመጣጣኝ ፈጣን ሽግግሮችን ከፍ ያሉ ጫናዎችን በሁለቱም የመጨረሻዎቹ ሜዳዎች እያየንበት የቀጠለው ጨዋታ 59ኛው ደቂቃ አርባምንጮች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ይሁን እንዳሻው ከማዕዘን ምት ያሻማትን ፀጋዬ አበራ በግንባር ገጭቷት በፍቃዱ አለማየሁ በሳጥን ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አህመድ ሁሴን ቢመታም ዳላንድ ኢብራሂም በንቃት አድኖበታል። ጥሩ ፉክክርን እያሳየን 70ኛው ደቂቃ ላይ የደረሰው ጨዋታ የአርባምንጭ ከተማው የግብ ዘብ እድሪሳ አጎጆጎ ኳስን ለማግኘት ሲል በከኮንኮኒ ሀፊዝ ግጭት በማስተናገዱ ለተጫዋቹ ህክምና እየተደረገለት ለአስር ደቂቃዎች ያህል ጨዋታው ለመቋረጥ ተገዷል።
ለተጨማሪ ህክምና ቶጓዊው ግብ ጠባቂ ወደ ሆስፒታል ካመራ በኋላ በተለይ ቡናማዎቹ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ብርቱ ጥረቶችን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አድርገዋል። ሲዲ ማታላ እና ኮንኮኒ ሀፊዝ በተመሳሳይ በግንባር ገጭተው በሚያስቆጭ መልኩ ያመከኑት እና እስራኤል ሸጎሌ ግልፅ የሆነ ጎልን አስቆጥሮ በዕለቱ ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ከተሻረበት አወዛጋቢ ውሳኔዎች በኋላ በመጨረሻም ጥረታቸው ሳይሳካ ጨዋታው አርባምንጭ ከተማ 1ለ0 አሸናፊ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ከመሪው መድን ጋር ነጥቡን በማጥበብ ለዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ያበላሸበትን ሽንፈት አስተናግዷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በጨዋታው የተነጋገርነውን አላደረግንም ያሉ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ ግን በሁለተኛው ላይ ቅያሪን በማድረግ ብልጫውን ይዘው መጫወት ቢችሉም እንደ ወትሮ አስፈሪ እንዳልነበሩ በመጠቆም የተሻረችዋ ጎል ግን ንፁህ ጎል እንደነበረች ራሱ ዳኛውም ቢያየው እንደሚሻል ገልፀው ተጫዋቾቼ ላደረጉት ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ ማንም ሳይጠብቀን እዚህ ደርሰናል ምንም ሳይሰስቱ ያላቸውንም ሰጥተዋል እግዚአብሔርንም ሆነ ደጋፊውን አመሰግናለሁ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ በረከት ደሙ በበኩላቸው የሚገኙበት የደረጃ ሰንጠረዥ ጥሩ እንዳልነበረ ከዛ ለመውጣት ደግሞ ከፍተኛ ብቃት ላይ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱም በጥንቃቄ ተጫውተው ማሸነፋቸውን ተጋጣሚያቸውም የነበረውን መከላከያ በጥንቃቄ ሰብረው ጎል በማስቆጠር ውጤት ይዘው ሊያጠናቅቁ እንደቻሉም ጭምር ተናግረዋል።