እጅግ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 0ለ0 በመለያየታቸው ዋንጫ የሚያነሱበትን ዕድል ሳይጠቀሙ ቀርተው ሌላ የጨዋታ ቀን ለመጠበቅ ተገድደዋል።
መድኖች ከሲዳማው ቡና የ3ለ0 ጨዋታ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን ያደረጉ ሲሆን አዲሱ ተስፋዬን በዋንጫ ቱት ፣ አለን ካይዋን በአብዲሳ ጀማል ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከስሑል ሽረው የ1ለ0 አሸናፊነታቸው ቢኒያም ፍቅሬን በሔኖክ ዮሐንስ በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሆኗል።
መድኖች ሊጉ ከሀያ ሰባት ዓመታት በፊት ሲጀመር በነጥብ ብልጫ በኤሌክትሪክ ያጡትን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማሳካት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚረዳቸውን ውጤት ለመያዝ በሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ መርሀ-ግብር በፌድራል ዋና ዳኛ ሀይማኖት አዳነ እየተመራ ተጀምሯል። መድኖች ዋነኛ ስርጭታቸውን አማካይ ክፍሉን አድርገው በይበልጥ ወደ መስመር ለጥጠው በመንቀሳቀስ ተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫውን ቢይዙም በመከላከሉ ረገድ ኮስታሮች የነበሩት ፈረሰኞቹ ሳጥናቸውን ለሀያ አምስት ደቂቃዎች ያክል ሳያስደፍሩ ቆይተዋል።
ለዚህም ማሳያው 7ኛው ደቂቃ ላይ ከያሬድ ካሳዬ በረጅሙ አብዲሳ ጀማል የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ መቶ ባህሩ ነጋሽ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ በጨዋታው የተደረገች ቀዳሚዋ ሙከራ ነበረች። የሽግግር አጨዋወትን ቢጠቀሙም አመርቂ ማጥቃቶችን ያላሳዩን ፈረሰኞቹ በተቃራኒው የጨዋታው ግለት ከፍ እያለ ሲመጣ በድግግሞሽ ጥቃቶች ተሰንዝሮባቸዋል። በ22ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ወገኔ አሻምቶ በረከት ካሌብ በግንባር ገጭቶ ባህሩ የያዘበት እና 24ኛው ደቂቃም የዕለቱ ዳኛ ሀይማኖት አዳነ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በፌር ፕለይ የሰጡት ኳስ በእጅ በእጁ አብረሀም ጌታቸው በመንካቱ ሳጥን ጠርዝ መድኖች ያገኙትን የቅጣት ምት አብዲሳ በቶሎ በአንድ ሁለት ከአቡበከር ጋር ተጫውቶ የመታትን ኳስ የግብ ዘቡ ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል።
ቀስ በቀስ የመድንን ጫና መቋቋም እየከበዳቸው የመጡት ፈረሰኞቹ በተከታታይ የግብ ሙከራዎች ለማስተናገድ ተገደዋል። 38ኛው ደቂቃ ዳዊት አሾልኮ የሰጠውን ረመዳን ወደ ላይ የሰቀለው እና ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሀይደር ከቅጣት ምት አሻምቶ አቡበከር በግንባር የገጫት እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ሻሂዱ ሙስጠፋ በወገኔ ገዛኸኝ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ቢመታውም በባህሩ ተጨርፋ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች።
ከዕረፍት መልስ ፈረሰኞቹ ፈጣን አጀማመርን ያሳዩበት ቢሆንም ከማጥቃት መሻሻል ውጪ ያደረጉት ከፍ ያለ እንቅስቃሴ በጠሩ ሙከራዎች መታጀብ የቻለ ግን አልነበረም። 47ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ዳግማዊ አሻምቶ አሸናፊ ጌታቸው በግንባር ገጭቶ ዒላማዋን ያልጠበቀችዋ ሙከራ በአጋማሹ ለሀያ ደቂቃዎች ያህል በወሰዱት ብልጫ ያደረጓት ደካማዋ ሙከራቸው ነበረች። ቀስ በቀስ እያደገ ወደ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የገባው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ከሳጥን ሳጥን ፋታ የሌለውን ማጥቃቶች አስተውለናል።
62ኛው ደቂቃ ፈሰኞቹ ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ከፀጋ ጋር ተቀባብሎ ፀጋ ወደ ቀኝ ለሔኖክ ዮሐንስ ሰጥቶት ተጫዋቹ በቀላሉ ያገኛትን አጋጣሚ የውጪው መረብ ላይ ለትሟታል ፣ ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ ሻይዱ በግንባር ገጭቶ አቡበከር ፍፁም ደካማ በሆነ የጊዜ አጠባበቅ ያመለጠውን ኳስ በድጋሚ ፈረሰኞቹ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ ወረድ ያለ መቀዛቀዝ ቢታይባቸውም ወደ መጨረሻው ሜዳ ይደርሱ የነበሩት መድኖች የቅዱስ ጊዮርጊስን መከላከል ግን ማስከፈቱ ቀላል አልሆነላቸውም ይልቁንም 66ኛው ደቂቃ ላይ ጎልን ለማስናገድ ተቃርበው ነበር።
ንጋቱ ገብረስላሴ ወደኋላ ለአቡበከር ለመስጠት ያጠረች ኳስን ፍፁም ፈጥኖ አግኝቶ ወደ ጎል ሲመታ ንጋቱ የሰራውን ስህተት ቢያርምም በድጋሚ ቢኒያም አግኝቶ ያደረጋት ሙከራን የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ መልሶበታል። መድኖች 68ኛው ደቂቃ ረመዳን የሱፍ ከያሬድ ካሳዬ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መቶ ባህሩ ከመለሰበት በኋላ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አንዳች ነገርን ከጨዋታው እንደፈለጉ የሚያሳይ ጫናዎችን ደጋግመው መድኖች ቢያደርጉም የባህሩ ነጋሽን መረብ መድፈሩ በእጅጉ ከብዷቸዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ አብርሀም ጌታቸው አቡበከር ሳኒ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከተወገደ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች እንደነበራቸው ብልጫ መድኖች ጎልን ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ መድን ዋንጫውን የሚያረጋግጥበትን ቀን ወደ ቀጣዮቹ ቀናት በይደር አቆይቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጋጣሚያቸው በሊጉ ጥሩ ቡድን እንደሆነ ጠቁመው ዋንጫን ለማረጋገጥ ሲሉ ያሳዩት እንቅስቃሴ ያንን የሚያሳይ እንደነበር ገልፀው ጥሩ ተነሳሽነት በቡድናቸው ላይ እንደታየ ለመለያ ክብር መዋደቅ ምን እንደሆነ ሜዳ ላይ ተጫዋቾቹ እንዳሳዩ እና በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው ነገር ግን የገኙ የጎል ዕድሎችንም ወደ ግብነት መለወጥ ተችሎ ቢሆን አሸናፊ መሆን ይችሉ እንደነበር ጨምረው ጠቁመዋል። የመድን አቻቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን በበኩላቸው ጨዋታው 0ለ0 አልቋል የሚቀሩ ሦስት ጨዋታዎች በመሆናቸው ዋንጫውን የማጣት ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው ቡድናቸው በዚህ ደረጃ መገኘቱ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምንም ነገር ሀሜት የፀዳ እና በጨዋታው ጠንካራ ሆኖ መቅረቡን ጠቁመው በመጨረሻም ቡድናቸው መደነቅ ሲገባው በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ የሚታየው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል።