ከወራጅ ስጋት ለመላቀቅ በምሽቱ የተገናኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከነማ ከብርቱ ፉክክራቸው በኋላ ዐፄዎቹ ተቀይሮ በገባው በረከት ግዛው አስደናቂ ጎል ታጅበው 1ለ0 በማሸነፍ እፎይታን ሲያገኙ ኤሌክትሪኮች ደግሞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።
ኤሌክትሪኮች ከንግድ ባንኩ የአቻ ውጤት በሁለት ተጫዋቾች ላይ ቅያሪ ሲያደርጉ አሸናፊ ጥሩነህን በአብዱላዚዝ አማን ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በሽመክት ጉግሳ ሲለውጡ በወላይታ ድቻ የ3ለ0 ሽንፈት ያስናገዱት ፋሲሎች በአምስቱ ላይ በወሰዱት ለውጥ ዮሐንስ ደርሶ፣ ዮናታን ፍሰሀ ፣ በረከት ግዛው ፣ ዳንኤል ፍፁም እና ቢኒያም ጌታቸው አርፈው ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ እዮብ ማቲያስ ፣ አቤል እያዩ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ማርቲን ኪዛ ተተክተው ገብተዋል።
በፌድራል ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት በሊጉ ለመቆየት እጅግ አስፈላጊ በነበረው የምሽቱ መርሀግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት የተጫወቱት ፋሲሎች በእንቅስቃሴም ሆነ በሙከራዎች ፍፁማዊ ብልጫን የወሰዱበት ነበር። በፈጣን ሽግግር ከመስመር በመነሳት ደጋግመው የኤሌክትሪክ የመጨረሻው ሜዳ አጋማሹን ያሳለፉት አፄዎቹ በጌታነህ ከበደ የጀመረው የ6ኛ ደቂቃ ዒላማዋን ባልጠበቀች የጭንቅላት ኳስ በኋላ አደገኛ ሙከራን ከአራት ደቂቃዎች በኋላ አድርገዋል። ኤሌክትሪኮች ከጨዋታ ውጪ በሚል ተዘናግተው ባለበት ወቅት ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ከቀኝ በኩል ወደ ሳጥን ይዞ የገባው አማኑኤል ገብረሚካኤል አክርሮ ሲመታ እድሪሱ አብዱላሂ ያያዘበት እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ መልስ አማኑኤል እና ጌታነህ ነካክተው የሰጡትን ማርቲን ኪዛ በእድሪሱ የተያዘበት አጋጣሚ የፋሲሎችን የማጥቃት ደመ ነብስ ያመላከቱን ሙከራዎች ነበሩ።
ከራሳቸው ሜዳ መውጣቱ የቸገራቸው እና ረጃጅም ያልተሳኩ ኳሶችን ለመጠቀም ውስን ጥረት በማድረግ 14ኛው ደቂቃ ሽመክት ከቀኝ አሻምቶ አቤል ሀብታሙ በግንባር ገጭቶ የግብ ዘቡ ፋሲል ከያዘባቸው ሙከራ በቀር በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በፋሲሎች ጫናዎች የበዙባቸው ኤሌክትሪኮች የግብ ጠባቂው እድሪሱ አብዱላሂ የግል ጥረት ባይኖር ኖሮ በርካታ ጎሎችን ቡድኑ ባስተናገደ ነበር። አቤል ከቀኝ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ይዞ የገባውን ኳስ ከግብ ዘቡ እድሪሱ ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀማት ፣ በ28ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የመጣች ኳስ በግንባር ተመልሳ ኪሩቤል ተቆጣጥሮ ወደ ውስጥ ሲያሻማ እዮብ በግንባር ገጭቶ እድሪሱ እና የግቡ ቋሚ ተባብረው ኳሷ ወደ ውጪ ልትወጣ ችላለች።
ከጨዋታው አንዳች ነገርን የፈለጉ የሚመስሉት ከወትሮው ከፍ ባለ ተነሳሽነት ማጥቃታቸውን ማሳደግን ያጠናከሩት አፄዎቹ ከማርቲን ኪዛ ሙከራ በኋላ 40ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ አደገኛ ሙከራ ሰንዝረዋል። ሀብታሙ ሸዋለም ሳጥኑ ጠርዝ አቤል እንዳለ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በአስደናቂ ምቱ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ብረትን ለትማ የተመለሰችው ከሁለት ደቂቃ መልስ ደግሞ ራሱ ጌታነህ ከአማኑኤል ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ሲመታው የኤሌክትሪክን የግብ በር በንቃት የጠበቀው እድሪሱ ያከሸፈበት የአፄዎቹ የአጋማሹ የመጨረሻ አጋጣሚ ሆና ጨዋታው ተገባዷል።
ኤሌክትሪክ አብዱላዚዝ አማንን በአብዱላሂ አላዩ ቀይረው በመከላከሉ ዕርምትን በወሰዱበት ሁለተኛ አጋማሽ ቡድኑ ከነበረው ደካማ እንቅስቃሴው ተሻሽሎ ከተጋጣሚው ጋር በመፈራረቅ ብልጫውን መያዝ የቻለበት ነበር። በተረጋጋ የኳስ ንክኪ 57ኛው ደቂቃ በረጅሙ በቀኝ ክፍሎ ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ መቶ ፋሲል ገብረሚካኤል ባወጣት ጠንካራ ሙከራንም በማድረግ ቀዳሚ መሆንም ችለዋል። ፍፁም ብልጫን ከወሰዱበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለተኛው በተጋጣሚያቸው ለመፈተን የተገደዱት አፄዎቹ በምኞት ደበበ እንዲሁም ኪሩቤል ከቅጣት አሻምቶ አማኑኤል ፣ ጌታነህ እና ምኞት ሳያገኟት በቀሩት ኳስ ዕድልን ለመፍጠር ጥረዋል።
ቡድኖቹ ቅያሪ ተጫዋቾችን በማስገባት በአዲስ ጉልበት ሦስት ነጥብን ለመጨበጥ በብርቱ በታገሉባቸው የመጨረሻዎቹ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ፋሲሎች 63ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ከማዕዘን ሲያሻማ ቢኒያም ገጭቶ እድሪሱ የያዘበት ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ በኤሌክትሪክ በኩል ከረጅም ርቀት አቤል ሀብታሙ ሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ በደረቱ አብርዶ ወደ ጎል መቶ ፋሲል ገብረሚካኤል በግሩም ሁኔታ አምክኖበታል። ቢኒያም ጌታቸው እና በረከት ግዛውን ወደ ሜዳ በማስገባት የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች እየተሳቡ ሲያጠቀሙ የነበሩት አፄዎቹ አብዱላሂ አሊዮ ተሳስቶ ቢኒያም በእድሪሱ ከመከነበት በኋላ በ85ኛው ደቂቃ ቢኒያም ጌታቸው ከግራ በኩች የግል ጥረቱን አክሎ ያቀበለውን ኳስ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያገኘው በረከት ግዛው እጅግ ማራኪ ጎልን በማስቆጠር ፋሳሎችን ያስፈነጠዘች ጎል በብዙ በሩን ሲመክት የነበረው እድሪሱ አብላሂ መረብ ላይ አሳርፏታል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታውን እንደሠሩት እና እንዳልጠበቁት እንዲሁም ተጫዋቾች ጥሩ እንዳልነበሩ ጠቅሰው ታክቲካሊ ጥሩ ስላልሆኑ እንደተሸነፉ ፣ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማግኘትም ትልቅ ነገር እንደሆነ እና የመትረፍ ተስፋቸውም እንዳልመነመነ ሲናገሩ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በሁለቱም ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደነበር ፣ በመጀመሪያው አጋማሽ የተገኙ ዕድሎችን አለመጠቀማቸው ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ተናግረው በዚህ ሰዓት ሦስት ነጥብ ትልቅ ዋጋ ቢኖረውም አንድ ነጥብ ትንሽ እንዳልሆነ ሆኖም ግን ሦስት ነጥቡ እንደሚገባቸው እና ይህ ድል እንደማያዘናጋቸው ገልጸዋል።