ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሲዳማ ቡናዎች በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያውን ዋንጫ ባሳኩበት ማግስት ደረጃቸውን ለማሻሻል ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ የሚረዳቸውን ድል ለማግኘት የሚፋለሙት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በአርባ ስድስት ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ሲዳማ ቡና በሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ የውድድር ዓመቱን ለማጠናቀቅ ድልን እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል።

ከቀናት በፊት ወላይታ ድቻን በማሸነፍ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት የሆኑት ሲዳማ ቡናዎች ብዙ ተጠብቆባቸው በውጣ ውረድ ያለፉትን የውድድር ዓመት ላይ የሊጉን ዋንጫ ባያሳኩም የኢትዮጵያ ዋንጫን በማንሳት ደጋፊያቸውን ክሰዋል። ከ24ኛው እስከ 31ኛው ሳምንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ላይ ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አራት ነጥቦች ሃያውን በማሳካት የውድድር ዓመቱ ጉዟቸውን ያቃኑት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐግብሮች በኢትዮጵያ መድን እና መቐለ 70 እንደርታ ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት በማገገም ነገ ድል ማድረግ የሚችሉ ከሆነ በሰንጠረዡ ቢያንስ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አላቸው። የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ተጫዋቾች ከታሪካዊው ድል ማግስት በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሜዳሊያቸውን ለማጥለቅ የሚያደርጉት ጉዞ እንዲሳካ ግን ባለፉት ሁለት የሊግ መርሐግብሮች ላይ ከፊት እና ኋላ የተስተዋሉባቸውን ድክመቶች ማረም ይጠበቅባቸዋል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል እንዲሁም ኳስ እና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት ጥምረት ወደ ቀደመ ብቃቱ መመለስም የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የቤት ስራዎች ናቸው።

ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር መውረዱን ባረጋገጠው ወልዋሎ ሽንፈት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን አርባ ሁለት በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው ያላቸውን ርቀት ወደ አራት ከፍ ማድረግ እና መጠነኛ እፎይታ ማግኘት የነገው ዋነኛ ዓላማቸው ነው።

በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ሽንፈት ቢገጥማቸውም ከዛ በፊት በተከናወኑ መርሐግብሮች በሜዳ እንቅስቃሴያቸው ላይም ሆነ ስነልቦና ረገድ መልካም ብቃት ላይ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ የነገው ዋና ዓላማቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች ባስመዘገቡበት ወቅት ያሳዩትን ብቃት ዳግም መመለስ ነው። ድሬዳዋ ከተማዎች የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለት ደረጃዎች ከፍ ማለት የሚችሉ በመሆኑ ውጤቱን እጅግ አጥብቀው ይፈልጉታል። ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ብሎ በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳለጥም በመጨረሻው ጨዋታ ላይ የተስተዋሉ የመከላከል እና የማጥቃት ድክመቶችን ማረም የሚጠበቅበት ሲሆን በተለይም በዕለቱ ለተጋጣሚ የመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ የነበረውና ሦስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። በሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር ውስን መቀዛቀዝ የተስተዋለበት የማጥቃት ጥምረቱም የአፈፃፀም ድክመቱን ማረም ይኖርበታል።

ሲዳማ ቡና ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ ሆኖ የነገውን ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ድልአዲስ ገብሬ እና አሕመድ ረሺድ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አቤል አሰበ ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።

ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሊጉ 23 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና 10 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 5 ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ረቷል፤ ቀሪዎቹ 8 የእርስ በርስ ግንኙነቶች በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና 25 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 17 ግቦችን አስቆጥረዋል።