ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊውን ሲዳማ ቡናን የወራጅነት ስጋት ከተጋረጠበት ድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው መርሐግብር ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።

ሲዳማ ቡና በ33ኛው ሳምንት በመቐለ 70 እንደርታ 1ለ0 ሲረቱ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ አስቻለው ሙሴ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ፣ አቤኔዘር አስፋው እና ደግፌ አለሙን በማሳረፍ በምትካቸው ደስታ ደሙ፣በዛበህ መለዮ፣ፍራውል መንግስቱ፣ ሬድዋን ናስር እና መስፍን ታደሰን ተክተው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማ በበኩላቸው በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ 3ለ1 ሲሸነፉ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል፤ አብዩ ካሣዬ፣አስራት ቱንጆ፣ ድልአዲስ ገብሬ፣ መስዑድ መሐመድ እና ዘርዓይ ገብረስላሴን አሳርፈው በምትካቸው አላዛር ማረነ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ሄኖክ ሀሰን፣ አቤል አሰበ እና ሐቢብ ከማልን ይዘው ገብተዋል።


ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ለሙሉጌታ ከበደ የአንድ ደቂቃ የሂሊና ፀሎት የተደረገላቸው የሳምንቱ የመጨረሻ ዕለት ቀዳሚው ጨዋታ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊውን ሲዳማ ቡናን በወራጅ ቀጠና ስጋት ውስጥ ከሚገኘው ከድሬደዋ ከተማ አገናኝቷል። ከፍተኛ የሆነ የግብ ማግባት ፍላጎቶች ከፈጣን ሽግግሮች ጋር እንዲሁም በአጫጭር ኳስ ቅብብል ጋር ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታው ወደ ፊት በሚደረጉ ሩጫዎች ግቦች የሚቆጠሩበት ቢመስልም ኢላማውን የጠበቀ ሁነኛ ሙከራ ሳያስመለክተን የመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ተቆጥረውበታል። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች በተለይም በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማግኘት ተቃርበው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ መመለከት ችለናል።

እምብዛም ከሙከራዎች ጋር መታጀብ ባልቻለው በጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ከሳጥን ውጪ ሆነው በሚያደርጉት ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ግልፅ የሆነ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር ግን አልቻሉም። ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ረጃጅም ኳሶችን ከተከላካይ ጀርባ እየጣሉ ብሎም በመስመር በኩል ሀብታሙ ታደሰን ኢላማቸው ያደረጉ ኳሶች ወደ ሳጥን እየጣሉ ቀዳሚ ለመሆን ሲጣጣሩ ብንልመለከትም ልክ እንደተገጣሚዎቻቸው ሙከራቸው አደገኛ መሆን ሳይችል ሲቀር በአጋማሹ አስተውለናል።

ሲዳማ ቡናዎች የኳስ ቅብብል ብልጫ በወሰዱባቸው በአጋማሹ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ምንም እንኳን የቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም የግብ እድል ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት የተቀዛቀዙበትን ደቂቃዎች ተመልክተናል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ጨዋታው ወሳኝ እና ከወረጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርጉት ትንቅን ከመሆኑም አንፃር ጠንከር ብለው ወደ ተጋጣሚ ቡድናቸው ግብ ክልል እየደረሱ ጫናዎችን እንዲሁም ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ 42ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው ያመከኑት አደገኛው ሙከራ ሲጠቀስ በጥሩ አንድ ለአንድ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ገብተው ቻርልስ ሙሴጌ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያለቀ ኳስ ለዩሐንስ ደረጀ አሻግሮለት ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ጠጠር ያለ ግብ ወደ ግብ ቢመታም ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ግብ ለማግኘት እጅጉን የተቃረቡበት ወርቃማው አጋጣሚ አይዘነጋም።

በድጋሚ 43ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የገቡት ብርቱካናማዎቹ  በአቡበከር ሻሚል ላይ በተሰራ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት የሲዳማ ቡናው የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነው ብርሃኑ በቀለ በአቡበከር ሻሚል ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷቸው ሀቢብ ከማል ወደ ግብነት ቀይሮ ብርቱካናማዎቹ በአጋማሹ መገባደጃ ላይ መሪ ሆነው የሚወጡበትን ወሳኝ የግብ ብልጫ አስገኝቶላቸው 1ለ0 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ሲዳማ ቡና የአንድ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ሲመለሱ ብርቱካናማዎቹ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሲዳማ ቡናዎቹ ጠንከር በተመለሱበት በሁለተኛው አጋማሽ በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ጥቃቶችን እያደረጉ የብርቱካናማዎቹን ተከላካይ መስመር ሲፈትኑ አስተውለናል። ብርቱካናማዎቹ ወሳኙን ነጥብ ይዘው ለመውጣት በጥንቃቄ ይጫወቱ እንጂ ጨዋታው 54ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የአቻነት ግብ አስተናግደዋል። ብርሃኑ በቀለ ከሳጥን ውጪ ሆኖ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አላዛር ማረነ በቀላሉ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ኳሱ አምልጦት ሐብታሙ ታደሰ ኳሱን በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ ሲዳማ ቡናዎችን አቻ አድርጓቸዋል።

የአቻነት ግቡ ያነቃቃቸው ሲዳማ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ወደ ሶስተኛው ሜዳ እየገቡ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ያስተዋልን ሲሆን 62ኛው ደቂቃ ላይ በመስፍን ታፈሰ አማካኝነት ያደረጉት አገደኛው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲጠቀስ ርቀት ላይ እግሩ ስር የተገኘውን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ ጠጠር ያለ ኳስ መጥቶ አላዛር ማረነ አግዶባቸዋል። ዘለግ ላለ ደቂቃ ወደ ፊት ሄደው ጫና ማሳደር የልቻሉት ብርቱካናማዎቹ የተጫዋች ቅያሪዎችን አድርገው ከረጅም ደቂቃ በኋላ 73ኛው ደቂቃ ላይ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል፤ ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሐመድ ያሻገረውን ኳስ ዩሐንስ ደረጄ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መስፍን ሙዜ እንዴትም አውጥቶባቸዋል።

75ኛው እና 77ኛው ደቂቃ ላይ አከታትለው ያደረጉት የሲዳማ ቡናዎቹ  ሙከራዎች ሲጠቀሱ አበባየሁ ሀጂሶ ርቀት ላይ ሆኖ የመታው ጠንከር ያለ ኳስ ከግቡ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ብሎ አልፎበታል፤ እንዲሁም መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ሳጥን ውስጥ የጣለውን ኳስ ሐብታሙ ታደሰ ያለቀ ኳስ አግኝቶ ቀላል በግንባር የተገጨ ሙከራ ወደ ግብ አሻግሮ ያመከነው አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር። በመልሶ ማጥቃት በቀለጠው ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በድጋሚ መሪ ለመሆን ግብ ሊያስገኝላቸው የሚችል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጣጣሩ እየተመለከትን ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ዘልቋል።

የጨዋታው መገባደጃ ላይ ቡድኖቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት ከሳጥን ሳጥን እየደረሱ የግብ እድሎች ለማግኘት አጋጣሚዎችን ሳጥን ውስጥ መፍጠር ቢችሉም አጋጣሚዎቹን ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸዋል በተለየም ብርቱካናማዎቹ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ያገኙትን ወርቃማ እድል አግኝተው አምክነዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በኳስ ቁጥጥር ጥሩ እንደነበሩ አንስተው በማስቆጠር ረገድ ግን ችግር እንዳለባቸው አንስተዋል ፤ በአንፃሩ የድሬዳዋ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ ተረፈ ሂርጳሳ በሰጡት አስተያየት በመጀመሪያው አጋማሽ በሚፈልጉት መንገድ እንደሄደላቸው አንስተው ፉክክሩ ከባድ ከመሆኑ አንፃር በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው የተሻለ ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።