አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የልጅ አባት በሆኑበት ዕለት የጣናው ሞገድ የጦና ንቦቹን 4ለ0 በመርታት ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል።
በፋሲል ላይ ከተቀናጁት የ3ለ0 ድል ድቻዎች በአምስት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን ሲያደርጉ መልካሙ ቦጋለ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ አብነት ደምሴ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ እና መሳይ ሠለሞንን በ አዛሪያስ አቤል ፣ አስናቀ አምታታው ፣ ቴዎድሮስ ታፈሠ ፣ ዘላለም አባተ እና ካርሎስ ዳምጠው ሲተኳቸው በአዳማ የ2ለ0 ሽንፈት የገጠማቸው ባህርዳሮች ሦስት ተጫዋቾችን ሲቀይሩ ፍፁም ፍትሕአለሙን በግርማ ዲሳሳ ፣ ፍሬዘር ካሳን በአምሳሉ ጥላሁን እንዲሁም አቤል ማሙሽን በወንድወሰን በለጠ በመተካት ቀርበዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ያለውን ቦታ ይዞ ለማጠናቀቅ ይረዳቸው ዘንድ ያደረጉት የሳምንቱ የማሳረጊያ መርሀ-ግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ መርጠው ከተንቀሳቀሱት የጨዋታ መንገድ ውጪ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን ያልተመለከትንበት ነበር። ወላይታ ድቻዎች በሽግግር ከሚመነጩ ኳሶቻቸው ከሁለቱም መስመሮች በኩል በጥልቅ እንቅስቃሴ ለመጫወት ባህርዳሮች በበኩላቸው በትዕግስት በቅብብል ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ማምራትን መርጠው መንቀሳቀስ ችለዋል። በ8ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ተሻምቶ ውብሸት ክፍሌ በግንባር ገጭቶ አቀብሎ ዘላለም አባተ በግንባር ገጭቶ ኳሷ ዒላማዋን መጠበቅ ካልቻለች ሙከራ በኋላ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማ ሳቢ ከነበረው ቅብብላቸው መልስ ጎል አግኝተዋል።
ፍሬው ከቀኝ ከቸርነት ጋር ተቀባብሎ ቸርነት ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት የወላይታ ድቻ የተከላካዮች አቋቋም ስህተት ታክሎበት በጥሩ ዕይታ የሰጠውን ኳስ ፍፁም ዓለሙ በመረብ አሳርፎ የጣናው ሞገድ መሪ አድርጓል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች እየተቀዛቀዘ በመጣው እንቅስቃሴ አጋማሹ ሊገባደድ በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች የባህርዳሩ አምሳሉ ጥላሁን በሁለት አጋጣሚዎች ከማዕዘን በቀጥታ አሻምቶ የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱ ካመከናቸው ተከታታይ ሙከራዎች በኋላ ከጎሉ ውጪ በጠሩ አጋጣሚዎች ያልጎመራው አጋማሽ ተገባዷል።
ወላይታ ድቻዎች ናትናኤል ናሲሩን በኬኔዲ ከበደ ዮናታን ኤልያስን በያሬድ ዳርዛ ለውጠው የሁለተኛው አጋማሽ አጀማመራቸው ጥሩ ቢመስልም የነበራቸው ፍፁም ደካማ መከላከል በፈጣን ሽግግር በሚጫወቱት ባህርዳሮች ጎል ያስተናገዱት 49ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። አምሳሉ ጥላሁን ከግራ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ያሻማትን ኳስ ተከላካዩ አዛሪያስ አቤል በአግባቡ በግንባር መግጨት የተሳነውን ኳስ ከጀርባ ሆኖ ያገኘው ወንድወሰን በለጠ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።
ወደ ጨዋታ ለመግባት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በባህርዳር ተጫዋቾች በፍጥነት ሲነጠቁ የሚስተዋሉት ድቻዎች የተጋጣሚያቸውን ጫና መቋቋም እየከበዳቸው ቀጥሎ በ64ኛው ደቂቃ በቅብብል ወቅት አዛሪያስ በድጋሚ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከእግሩ ስር ኳስን ያገኘው ወንድወሰን በለጠ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ካከለ ከሁለት ደቂቃ መልስ ደግሞ በረከት ጥጋቡ መሐል ለመሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ የግብ ዘቡ ቢኒያም ለማውጣት የመታት ኳስ በኬኔዲ ከበደ ተደርባ የተመለሰችን ኳስ ወንድወሰን በለጠ ሦስተኛዋን የሀትሪክ ግቡን በጥሩ አጨራረስ ከመረብ አዋህዷል። በቀጣይ ደቂቃዎች በ71ኛው ላይ የጦና ንቦቹ በኬኔዲ ከበደ ከሰነዘሩት ሙከራ በስተቀር ጨዋታው በባህርዳር ከተማ የ4ለ0 ድል ተጠናቋል።
ከጨዋታው መቋጫ በኋላ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በጨዋታው ጥሩ እንዳልነበሩ የገባባቸውን ጎል ከዕረፍት ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግዱው ጎል በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም በመከላከሉ ተጫዋቾቻቸው የሰሯቸው ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈላቸው እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ደግሞ ቡድናቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልፀዋል። የባህርዳር ከተማው ረዳት አሰልጣኝ ደረጀ መንግስቱ በአንፃሩ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር በመግለፅ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ በቡድኑ በነበረው መነሳሳት እና ፍላጎት የተነሳ ውጤት ይዘው እንደወጡ የተጋጣሚያቸውን ረጃጅም ኳስን በመቆጣጠር የተሻለ ስራን በመስራት ውጤት ይዘው ሊወጡ እንደቻሉ ጠቁመዋል።