ወልቂጤ ከተማ ወደነበርኩበት ፕሪሚየር ሊግ ልመለስ ይገባኛል ሲል ጠየቀ

ወልቂጤ ከተማ ወደነበርኩበት ፕሪሚየር ሊግ ልመለስ ይገባኛል ሲል ጠየቀ

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ላይ በደመወዝ ጥያቄ ከሊጉ የተሰረዘው ወልቂጤ በቀጣዩ የ2018 የውድድር ዘመን ልመለስ ይገኛል ሲል በደብዳቤ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅቶችን ካደረገ በኋላ ለውድድር ወደ ድሬዳዋ ቢያመራም በክለቡ የተለያዩ ክሶች እና ውዝፍ የደመወዝ ክፍያዎች ስለነበሩበት በመጨረሻም ከተከታታይ የፎርፌ ውጤቶች በኋላ ከሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ ዕርከን ወርዶ በከፍተኛ ሊጉ ቆይታ ቢኖረውም የኋላ ኋላ ግን በመጨረሻም ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱ ይታወሳል ፣ ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እየታዩ ከሚገኙ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ክለቡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ልመለስ ይገባኛል ሲል በተከታዩ ደብዳቤ ሀሳቡን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቁሟል።

ሙሉው የደብዳቤው ሀሳብ 👇

“በኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን ክለቦችን የሚያስተዳድርበት ስርአት ከፍ ለማድረግ የክለብ ላይሰሲንግ መመሪያ በማውጣት ከምዝገባ ጀምሮ ክለቦች የዝውውርና የውድድር ፍቃድ የሚያገኙበት ስርአት ዘርግቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሚካፈሉ ክለቦች በ5 መሰረታዊ መስፈርቶች ስር ዝርዝር መስፈርቶች ከቅጣት ማእቀፎች ጋር በማውጣት ምዝገባ ያከናወነ ሲሆን የወልቂጤ ከተማ እግር ካስ ክለብ ግን የደመወዝ ውዝፍ እዳ ስላለብን መስፈርቱን በወቅቱ ባለሟሟላታችን የውድድር ፍቃድ ባለማግኘታችን እንወዳደርበት ከነበረው ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ባስተዳደራዊ ውሳኔ ወደ ከፈተኛ ሊግ ወርደን እንድንሳተፍ ኢ ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔ ተላልፎብናል፡፡

ሆኖም ክለባችን ውዝፍ ደመወዝና እዳ ባለሟሟለላቱ በክለብ ላይስሲንግ መስፈረት መሰረት ማለትም፡- ‘ክለብ ከደመወዝና ሌሎች ውዝፍ እዳዎች ነፃ መሆን ይኖርበታል እስከ ቀነ ገደቡ መስከረም 8/2017/ድረስ ተግባራዊ ካልተደረገ የውድድር አመቱን 3 ነጥብ ተቀነሶበት የሚጀምር ይሆናል በተጨማሪም ምንም አይነት የተጫዋች ውል ማጽደቅ አይቻልም።’

በሚለው መስፈርት መሰረት የውድድር አመቱን ስንጀምር 3 ነጥብ ተቀንሶብን መጀመር ሲገባን ከክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ እንዳልተሰጠን እየታወቀ ፕሮግራም አውጥቶ ፎርፌ መስጠት በእኛ በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በወቅቱ ብንገልፅም ሰሚ ሳነገኝ ቀርተን የሚጠበቅብን 641,000 ዶላር እና 12,000(አስራ ሁለት ሺ CHF/የስዊዝ ፍራንክ ከፍለን ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርደን እንድንወዳደር ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን በተጫዋች ተግባቢነትና በፋይናንስ አጠቃቀም ዙሪያ በታዩ የአሰራር ግድፈቶች ምክንያት የፌዴሬሽን ዲሲፒሊን ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ህጉን የጣሱ ክለቦች ከ2 ጨዋታ በላይ በፎርፌ ተሸናፊ ሆነው ሳለ ከሊጉ አይወርዱም ብሎ የፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መወሰኑን ከሰጡት መግለጫ መገንዘብ ችለናል፡፡ ታዲያ ይሄ ከሆነ የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፎርፌ ተሰጥቶበታል ተብሎ ለምን እንዲወርድ ተደረገ? የሚለውን ጥያቄ አጭሮብናል። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ሁሉንም ክለቦች በአንድ አይን ተመልክቶ ክለባችን ወደ ነበረበት ፕሪሚየር ሊግ እንዲመለስ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጠን እናመለክታለን፡፡”