በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚካፈለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት በሊጉ ላይ ቆይታ የነበረውን አሰልጣኝ ምርጫው ለማድረግ ተቃርቧል።
የ2017 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን በ43 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የውድድር ዘመኑን ያጠናቀቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ መሪነት ላለፉት አራት የውድድር ዘመናትን ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ግን በአዲስ አሰልጣኝ ለመመራት ክለቡ በመወሰኑ ወጣቱን አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻን ምርጫው አድርጎ የተሳካ ንግግር ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ውስጥ የስልጠናውን ዓለም በይበልጥ ያዳበረው አሰልጣኙ በርካታ ወጣት ዕንስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከሀገሪቱ እግር ኳስ ጋር ያስተዋወቀ ሲሆን በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ የቦሌ ክፍለ ከተማ የሴቶች ቡድንን በመያዝ በፕሪምየር ሊጉ ተፎካካሪ ቡድንን ገንብቶ አስመልክቶናል። ቀጣዩን ዓመት ግን ዘለግ ካለው የቦሌ ቆይታው በኋላ አዲስ ማረፊያውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለማድረግ ስለመቃረቡ ዝግጅት ክፍላችን አረጋግጣለች።
ስምምነቱ በተሳካ ሁኔታ የሚጠናቀቅ ከሆነም ከፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ጀምሮ በሚከፈተው የዝውውር መስኮትም አሰልጣኙ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመቀላቀል ስራቸውን እንደሚጀምሩም ሰምተናል።