አሰልጣኝ በሽር አብደላ ሸገር ከተማን በፕሪሚየር ሊጉ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚመሩት ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ በ2018 የውድድር ዘመን ከሚካፈሉ ሃያ ቡድኖች ውስጥ አንዱ በመሆን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የምንመለከተው ሸገር ከተማ ከወጣቱ አሰልጣኝ በሽር አብደላ ጋር ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዘመናት እንዲያሳልፍ መወሰኑን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሸገር ከተማን በያዘበት የመጀመሪያው ዓመት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያሳደገው አሰልጣኝ በሽር የተጫዋችነት ዘመኑን በደደቢት ፣ ወልቂጤ ፣ መቂ እና በትውልድ ሀገሩ ነገሌ አርሲ አድርጎ በመጨረሻም በጉዳት ካቆመ በኋላ በነገሌ አርሲ ረዳት አሰልጣኝ ከመሆን አንስቶ በዋና አሰልጣኝነትም ጭምር ቡድኑን በመምራት በተከታታይ በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በማድረግ ጥሩ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሸገር ከተማን በመያዝ በመጀመሪያ ዓመቱ ወደ ከፍተኛው የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን ማሳደግም ችሏል።
አሰልጣኙን በሊጉ ማቆየቱ የተረጋገጠው ቡድኑ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ቅድመ ስምምነቶችን ማድረግ የጀመረ ሲሆን የዝውውር መስኮቱ ሲከፈትም በይፋ ውላቸውን እንደሚያፀድቅም ዝግጅት ክፍላችን ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።