“ከምስረታ እስከ ፕሪምየር ሊግ ድል” የኢትዮጵያ መድን የድል ጉዞ

“ከምስረታ እስከ ፕሪምየር ሊግ ድል” የኢትዮጵያ መድን የድል ጉዞ

የኢትዮጵያ መድን ከምስረታ እስከ ሊጉ ቻምፒዮንነት በወፍ በረር ሲቃኝ !

በ1974 መጨረሻ ዓ.ም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከዚያ በፊት በመላ አገሪቱ የነበሩ ክለቦች ፈርሰው በአዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት 50 ቡድኖች እንዲመሰረቱ አዘዘ፡፡ ከ1970ዎቹ አጋማሽ ቀደም ብሎ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመንግስት ስር አልነበሩም፡፡ ይህን ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋማትም በግል ባለሃብቶች ይተዳደሩ ነበር፡፡ ከአብዮቱ ማግስት በኋላ ግን እነዚህ ድርጅቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ስለዚህ የፋይናንስና ኢንሹራንስ ድርጅቶች የሆኑት ባንክና መድንም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተግባራዊነቱን በሚቆጣጠረው የአዋጁ ተፈጻሚነት መሰረት ቡድን ማቋቋም ተጠበቀባቸው፡፡ መድንም ያኔ ተቋቋመ፡፡ ክለቡ ከመመስረቱ በፊት ግን ተጫዋቾች ማሰባሰብ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ማዋቀር ነበረበት፡፡ ከዓመታት በፊት ኢንሹራንስ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሁለት ታዋቂ ተጫዋቾች – ቆይቶም አሰልጣኞች የሆኑ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ታላቁና ስመጥሩው መንግስቱ ወርቁ እና ካሳሁን ተካ፡፡


መንግስቱ ወርቁ በ1958 መደበኛ የሽያጭ ሰራተኛ ሆኖ በአንበሳ ኢንሹራንስ ውስጥ ትልቅ ግልጋሎት ሰጥቷል፡፡ በነበረው ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍና የሥራ ታታሪነት ከድርጅቱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ1960ዎቹ ዓመታ “ ሠራተኛንና ሥራን ማገናኘት ” በሚለው መመሪያ መሰረት ስፖርት ኮሚሽን እንዲመደብ ትዕዛዝ ሲደርሰው ከመድን ጋር መለያየቱን በ1986 ዓ.ም “መድን ኢንተርናሽናል” በተሰኘ መጽሄት ተገልቷል፡፡ በዚያ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን መልሶ ማቋቋም ይጠበቅበታልና ወደዚያው (ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ማቋቋሙ ሥራ) አመራ፡፡ እናም ካሳሁን ተካ መድንን በአሰልጣኝነት የማዋቀር ኃላፊነት ተጣለበት፡፡ በ1974 ትግል ፍሬ፣ አብዮት ፍሬ፣ እርምጃችን፣ ወደፊት፣… እና ሌሎችም ቡድኖች ሲፈርሱና ካሳሁን መድንን ማደራጀት ሲጀምር ከፈረሱት ክለቦች ውስጥ በርካታ ተጫዋቾች ክለቡን ተቀላቅለውታል፡፡ በተለይ የአብዮት ፍሬ ብዙሃኑ ተጫዋቾች መድን ምርጫቸው ሆኖ ነበር፡፡ ይህን በማስመልከት ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ “ክለቡን ያቋቋምኩት እኔ ነበርሁ፡፡ ተጫዋቾችን በአግባቡ መለመልሁ፡፡ በጣም የተደራጀ ቡድን (Solid Team) ሰራን፡፡” ብሏል ለሶከር ኢትዮጵያ – የአሰልጣኞች ገጽ በሰጠው ቃለ መጠይቅ፡፡

በቀደመው ዘመን መድን ይከተል በነበረው ማራኪ የጨዋታ ሥልት ሳቢያ በርካታ ማነጻጸሪያ ተቀጽላ መጠሪያዎች አግኝቷል፡፡ ሜዳ ላይ ከየትኛውም ተጋጣሚዎቹ ጋር ሲጫወት በሚተገብረው ውብ አጨዋወት የተነሳ በደጋፊዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሰርክ ታዳሚያን ዘንድ “ሊቨርፑል” እስከመሰኘት ደርሷል፡፡ ከምስረታው ጀምሮ ቡድኑ ውስጥ ብዙ ቴክኒሺያን ተጫዋቾች ነበሩት፡፡ መድን ከ1970ዎቹ አጋማሽ በኋላ ከሌሎች የአንደኛ ዲቪዚዮን ጠንካራ ቡድኖች ጋር የሚያደርገው ጨዋታ እጅጉን ማራኪ እንደነበር አያሌ የዚያ ዘመን እግርኳስ ተመልካቾች እንዲሁም አንጋፎቹ የእግርኳስ ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

አሰልጣኝ ካሳሁን ተካም ይህን ሐሳብ ይጋራል፡፡ የአሰልጣኝነት ህይወቱን በተመለከተ ከአራት ዓመታት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ – የአሰልጣኞች ገጽ – አምድ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ “ ያ መድን “የእሁድ ፕሮግራም!” ይባል ነበር፡፡ (በጊዜው ታዋቂው የነበረውን የኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ያስታውሷል!) ዘመናዊ እግርኳስ ነበር የሚጫወቱት፡፡” ሲል ያክላል አሰልጣኝ ካሳሁን፡፡

ከ1970ዎቹ አጋማሽ አንስቶ መድን በቴክኒካዊ ክህሎት ለታደሉ ተጫዋቾች ቅድሚያ ይሰጥ እንደነበር ይነገራል፡፡ ካሳሁንም ይህን ያረጋግጣል፡፡ በ1970ዎቹ መጨረሻ ክለቡን ስለተቀላቀለው አስደናቂ አማካይ በማውሳት ሃሳቡን ያጠናክራል፡፡ “ የአዲስ ብስራት ወንድም የነበረው አብርሃም ብስራትን ከፋብሪካ ቡድኖች ነው ያገኘሁት፤ በጣም ቀጭን ስለነበር የአስተዳደር ሰዎች ” ይሄ አሁን በምን እግሩ ነው ኳስ የሚመታው? ልትሰብረው እንዴ!” ሲሉኝ ” ስለሱ አታስቡ!” ብያቸው ውድድሩ ተጀምሮ ሲጫወት ሲያዩት ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ እሱ የያዘውን የተጋይነት መንፈስ ማንም አልነበረውም፡፡ ብዙ ብቃቶች ነበሩት፡፡ ረጃጅም ቅልጥሞች አሉት፤ ኳስ ያስጥላል፤ ቴክኒሺያን ነው፤ ግብ ያስቆጥራል፤…..ከዚያ ብሄራዊ ቡድን ተመረጠ፡፡ ተጫዋቾች ወደ ጣልያን ሲጠፉ እኔ ገብቼ የተጫወትኩ ዕለት ነው እርሱም አብሮ የጠፋው፡፡ በመድን እሱን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ብዙ ነበሩ፡፡” ብሏል፡፡

በ1976 መድን ከሲሚንቶ ጋር ያደረገው ጨዋታም ከብዙሃኑ አእምሮ እንልወጣም ይናገራል፡፡ “በወቅቱ ሲመንት የተባለው ቡድንም እጅግ ጠንካራ ተፎካካሪ ስለሆነ የሁለቱ ጨዋታ ኳስ የመልስ ምት የሚሆንበትን አጋጣሚ ለማግኘት አስቸግራል፡፡ በቃ የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታ (Pink-Ponk) ይመስልሃል፡፡ ይህ ጨዋታ መድኖች ምን ያህል ማራኪ አጨዋወት ይተገብሩ እንደነበር ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በጨዋታው የእጅ ውርወራና የመልስ ምቶች በብዛት ያልታዩበት፣ ደጋፊዎች በክፍተኛ ጉጉት ቁጭ-ብድግ ብለው ውብ እግርኳስ የታደሙበት፣ ተጫዋቾች የኳሱን ፍሰት እንዳሻቸው የተቆጣጠሩበት ምሽት አሳልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ዋንጫውን መድኖች በፍጹም ቅጣት ምት ተሸንፈው አጥተዋል፡፡ ልጆቹ ትክክለኛውን ስልጠና አግኝተዋል፡፡ አንድ ጊዜ እንደማስታውሰው እሁድ ዕለት ጊዮርጊሶች ቡናን 2-0 ረቱና ” Home made Brazil!” ተብሎ ተጻፈላቸው፡፡ ከዚያ ከእኛ ጋር ሲደርሳቸው 6-2 ረመረምናቸው፡፡ መንግስቱ አስተማሪዬ ስለነበር ምን ይዞ እንደሚመጣ ስለማውቅ እኔ በደንብ ተዘጋጅቼ ቀረብኩና ትልቅ ድል አስመዘገብን፡፡

በመሃል ጀርመን ሀገር ሄጄ ስመለስም ብዙ ነገሮችን አስተምሬያቸዋለሁ፡፡ የዛኔም ጥሩ ይጫወቱ ነበር፡፡” ይላል የክለቡ መስራችና የመጀመሪያ አሰልጣኝ፡፡ “የተጫዋቾቹ መለያም ተመሳሳይነት ስለነበረው መድን በወቅቱ አርጀንቲና ይባልም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እኛ ነበርን የመለያውን አይነትና ቀለም የምንመርጠው፡፡” ሲልም ያክላል፡፡

ታላቁ መንግስቱ ወርቁም ብ1980 መድንን ለማሰልጠን የወሰነው በዚያን ጊዜ በቡድኑ ውስጥ የተያዙት ተጫዋቾች ችሎታ በመደመሙ እንደነበር ገልጧል፡፡ ያንን እምቅ አቅም ለማጎልበት እንዲሁም በቡድኑ አጨዋወት ላይ ያስተውላቸው በነበሩ መጠነኛ ታክቲካዊ እንከኖች ላይ ማሻሻያና ዕርማት በማድረግ ቡድኑን ታላቅ ቦታ የማድረስ አላማ አንግቦ ክለቡን ለማሰልጠን እንደበቃ ለ“መድን ኢንተርናሽናል” መጽሄት የዛሬ ሠላሳ ሁለት አመት ገደማ ተናግሯል፡፡“ በአሰልጣኝነት ሙያዬ በከፍተኛ ደረጃ የደከምኩበትና ያለኝን እውቀት በሙሉ ያፈሰስኩት በመድን ቡድን ላይ እንደሆነ አስታውሳለው፡፡ ይህን ለማድረግ ያነሳሳኝም በመድን ውስጥ የነበሩት ተጫዋቾች ድንግል መሬት ሆነው ስላገኘኋቸው ነበር” ብሏል፡፡

መድን ባለፉት አርባ ዓመታት ከሌሎች ክለቦች በተለየ ተጫዋቾችም ሆነ አሰልጣኞች ላይ የአጨዋወት ስልትን በሚመለከት ጫና ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ መድን በየዘመኑ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾችን የማፍራት የበርካታ ዓመታት ልማድ አዳብሯል፡፡ በተለይ ግላዊ ክህሎታቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን መድን ውስጥ ማየት እንግዳ ያልነበሩባቸው የውድድር ዘመናት ብዙ ናቸው፡፡ ዐቢይ ነጋሽ፣ ሲራክ ዮሃንስ፣ ጌቱ መልካ፣ አብርሃም ብስራት፣ ደረጀ ጌታቸው፣ አብዱላሂ ሰኢድ (አብዲ)፣ ተክሌ ብርሃኔ፣ ሀሰን በሽር፣…..መጥቀስ ይቻላል፡፡

ክለቡ ከምስረታው ዘመን አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ታችኛው ሊግ እስከወረደበት 1990ዎቹ አጋማሽ (1996 መጨረሻ) ድረስ በነበሩት ሁለት አስርት በርካታ ውጣ-ውረዶችን አሳልፏል፡፡ ሜዳ ላይ ማራኪ አጨዋወትን ከማሳየት እንዲሁም ቴክኒካዊ ክህሎት የተላበሱ ተጫዋቾችን ከማፍራት ግን ቦዝኖ አያውቅም፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አስርት የተጠጉ ዘመናት ደግሞ መድን የቀደመ ገናናነቱ አብሮት አልነበረም፡፡ እነዚህኞቹ ዘመናት በፕሪምየር ሊጉና በሱፐር ሊጉ ሲዳክር የነበረባቸው የክለቡ አስቸጋሪ አመታት ናቸው፡፡ (በ2002 እና 2006 ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱን ይታወቃል፡፡ 2003፣ 2004፣ 2007-2014 ድረስ – በከፍተኛ ሊጉ መክረሙን ልብ ይሏል፡፡)

የአገሪቱን ድርጅት-አገዝ የእግርኳስ ክለቦች አደረጃጀት እና የበጀት እገዛ ታሪክ ላጤነም አካል ይህ ቡድን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች በተሻለ እድለኛ እነደነበር መረዳት አያዳግትም፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለእግርኳስ ክለቡ ከምስረታው ጀምሮ የተጠናከረ የበጀት አቅም ፈጥሮለታል፡፡ የራሱ (የቡድኑ) ሜዳና ተጫዋቾች የሚኖሩበት ደረጃውን የጠበቀ ማረፊያ እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ቡድኑ በአግባቡ የሚዘጋጅለትን የልምምድ መርኃ ግብር በራሱ ሜዳ ይከውን ነበር፡፡ ያኔ ሌሎች ቡድኖች የተሟላ የእግርኳስ መሰረተ-ልማት አልነበራቸውም፡፡ ለሥልጠና እንኳ እንጦጦ፣ ኮተቤና ሌሎችም የከተማዋ ጫካዎች እየሄዱ ነበር ልምምድ የሚሰሩት፡፡ መድን በዚህ ረገድ ችግር ገጥሞት አያውቅም፡፡ ከአገሪቱ ስታንዳርድ አንጻር ቃሊቲ አካባቢ ለልምምድ በቂ የሆነ ሜዳ ነበረው፡፡ (ሜዳው ለከፍተኛ ሊግ ውድድሮች እና በተመሳሳይ ሰዓት ይደረጉ ለነበሩ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማከናወኛ ይውል እነደነበር ያስታውሷል፡፡)

ለተጫዋቾቹ በካምፕ ውስጥ ይቀርብላቸው የነበረው ምግብም በባለሙያዎች የተጠናና የተዘጋጀ እንደነበር ይነገራል፡፡ ክለቡ ሲመሰረት አካባቢ የነበረውን ሁኔታ አሰልጣኝ ካሳሁን ሲያስረዳም “ለተጫዋቾቹ የሚቀርበው የተመጣጠነ ምግብ ሲሆን እኔ ራሴ በስነ-ምግብ ባለሙያዎች (Nutritionists) አማካይነት የምግብ አይነቶች ዝርዝር (Menu) እንዲዘጋጅ አድርጌ በዚያ መሰረት ይመገባሉ፡፡ ለጨዋታ ወደ ናዝሬት ስንሄድ የምንመገበውም አዳማ ራስ ሆቴል ሲሆን ሌሎች ግን ከተማው ውስጥ ያሉ አነስተኛ ምግብ ቤቶችን ይጠቀማሉ፡፡ አንዳንዴ ሥራ አስኪያጃችን መኢሰማ (መላው ኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር) ውስጥ ያሉ ካድሬዎች እንዴት ነው ይሄ ነገር? የወዛደሩን ሞራል ለመንካት ነው ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ፥ የምን ሞራል መንካት አመጣችሁብኝ? ገንዘብ ካለን እኮ የፈለግንበት መመገብ እንችላለን፡፡ ይላቸዋል፡፡ ” በማለት ያስታውሳል፡፡

ክለቡ ተጫዋቾችን ከሌሎች ክለቦች ለማዛወርም በቂ ገንዘብ የማውጣት ችግር አልነበረበትም፡፡ ጥራት ባለው የትጥቅ አቅርቦት፣ ለተጫዋቾችና አሰልጣኞች በሚከፍለው ደመወዝ፣ በፊርማ ክፍያ፣ ለታዳጊና ተተኪ ተጫዋቾች ለሚያፈሩትና በታችኛው እርከኖች ለሚይዟቸው ቡድኖች (ሲ-ቡድን፣ ቢ-ቡድን) በሚሰጡት ትኩረት ፈርጠም ያለ የገንዘብ አቅም እንደነበራቸው መረዳት ይቻላል፡፡
አሰልጣኝ ካሳሁን ክለቡ በምስረታው ወቅት በበጀት ጉዳይ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠመውም ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ “የክለቡ አመራሮችም መድን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛና ተባባሪ ነበሩ፡፡ በተለይ የመጀመሪያው አስተዳዳሪ እጅግ በጣም ጥሩ ሰው ነበር፡፡ በ1970ዎቹ አጋማሽ የትኛውም ክለብ የ ምርት የሆኑ መለያዎችን ሳይለብስ እኮ ነው የእኔ ቡድን ደረጃቸውን የጠበቁ የዚህ <ካምፓኒ> ማሊያዎችን ይለብስ የነበረው፡፡ የልምምድ ትጥቁና ጫማውም ከምዕራብ ጀርመን ነበር የሚመጣላቸው፡፡ ሰራተኛ ቡድኑ እንኳ የ ምርት እንዲጠቀም ፈቅዷል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ይሄ “የከበርቴ ቡድን/(Feudal Team) እያሉ ይጠሩናል፡፡ በኢንሹራንሱ ዘርፍ የጠለፋ ዋስትና ሽፋን የሚሰጡ አካላት (Re-Inssuers) አሉ፡፡ አንድ ጊዜ ከእነዚህ አካላት አንደኛ የሆነው ሚሪ ከሪ የሚባል ድርጅት ከሚንስክ “ምን ይጠየቅላችሁ?” አለን፡፡ “ጫማ፣ ቱታና ደረቱ ላይ <መድን> የሚል የክለቡ መጠሪያ የታተመበት መለያ ይምጣልን፡፡”ብለን ነገርናቸው፡፡ ተሰርቶ መጣ፡፡ ካምፑ ውስጥ እንኳን የሚጫሙት <ስኒከር> እንጂ እንደ ሌሎቹ ነጠላ ጫማ አልነበረም፡፡ እኔም በነበረኝ አቅም ክለቡ በሁሉም ዘርፍ “ፕሮፌሽናል” እንዲሆን በትልቁ ጥሬያለሁ፡፡ ከዚያ ቡድኑ የሁሉንም ትኩረት ሳበ፡፡” በማለት ሐሳቡን ይሰጣል፡፡

መድን በ1984 በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው የአንደኛ ዲቪዚዮን የእግርኳስ ውድድር (አንድ ግጥሚያ እየቀረው) ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ስለነበር በቀጣዩ ዓመት በሚካሔደው ሁለተኛው የአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ (ካፍ-ካፕ) ላይ እንዲሳተፍ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፈቀደ፡፡ በጊዜው በአህጉሪቱ የክለብ ውድድሮች አገሩን ወክሎ እንዲሳተፍ ከእግርኳስ ማህበሩ ያገኘው ይሁንታ ክለቡን በቀጥታ ወደ ዝግጅት እንዲያመራ ገፋፋው፡፡ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት የተጣለበት ይህ ቡድን ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በከፍተኛ የህብረት ሥራ ጥንቃቄ የታከለበት ጥሩ ዝግጅት አደረገ፡፡ ለክለቡ የመጀመሪያ አህጉራዊ ተሳትፎ በመሆኑ እግርኳሱ የሚመለከታቸው የክለቡ አባለት በሙሉ ማለትም – የበላይ አመራሮች፣ የስፖርት ኮሚቴ አባላት፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት መድን የተሻለ ውጤት ያስመዘግብ ዘንድ ተረባረቡ፡፡ መድን በአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ (ካፍ-ካፕ) ውድድሩ ላይ ያሳየው ብቃት አስገራሚ ነበር፡፡ በመድን የ1985/1986 የካፍ ካፕ የመጀመሪያ ተመክሮ መድን በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ታላቅ የሚባል ገድለ ፈጸሙ፡፡ ከኪጋሊ እስከ አቢጃን በዘለቀው የክለቡ ጉዞ መድኖች ለአገራቸው ሌሎች ክለቦች በተምሳሌትነት የሚወሳ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ በአንጻሩ በ1985 እጅጉን ተዳክመው የቀረቡበትን የሃገር ውስጡን የብሄራዊ ዲቪዚዮን ሻምፒዮናም የዊንድሆኩን ጨዋታ ከማከናወናቸው በፊት መውረዱን ካረጋገጠው ኪራይ ቤቶች ጋር ተፋልመው ኢሳይስ ገ/የሱስ መጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት የድል ግብ 2-1 አሸንፈው ከመውረድ ድነዋል፡፡

መድን ከአርባ ዓመታት በላይ በሚቆጠር ታሪኩ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸውን ታላላቆቹንና አንጋፎቹን የአገር ውስጥ አሰልጣኞች በሙሉ ቀጥሯል፡፡ (ከሰውነት ቢሻውና ከማል አህመድ ውጪ) ከምስረታው ጊዜ አንስቶ ካሳሁን ተካ፣ ወርቁ ደርገባ፣ ሪኮ ጂላርዲ፣ መንግስቱ ወርቁ፣ ስዩም አባተ፣ ሐጎስ ደስታ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል፣ ብርሐኔ ገ/እግዚኣብሄር፣ ንጉሴ ገብሬ፣ ወንድማገኝ ከበደ፣ በኃብቱ ገ/ማርያም፣ አስራት ኃይሌ፣ ጌታሁን ገ/ጊዮርጊስ የመድን አሰልጣኞች ሆነዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ጥላሁን መንገሻ፣ አብርሃም መብራህቱ፣ መርሻ ሚደቅሳ፣ ገ/መድን ኃይሌ፣ ክፍሌ ቦልተና፣ አባይነህ ማሞና ደረጄ በላይ የክለቡ አሰልጣኞች ነበሩ፡፡ ወጣቶቹ ያሬድ ቶሌራና በጸሎት ልዑልሰገድ ደግሞ በቅርብ ዓመታት በመድን አሰልጣኝነት ሰርተዋል፡፡

በግንቦት 10-2000 ዓ.ም. በወጣ የኢንተር ስፖርት ጋዜጣ-ቁጥር 451 እትም ላይ የቀድሞው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ኤርሚያስ አማረ ይህን የክለቡን ያልተረጋጋ የአሰልጣኞች ሹም-ሽር ” መድን እንደ ሪያል ማድሪድ” በሚል ርዕስ ጥሩ ዘገባ ሰርቶበታል፡፡ ኤርምያስ ተደጋጋሚውን ቅጥር በማስመልከት ከሰበሰባቸው ማስረጃዎች ተነስቶ ክለቡ በአንድ አስርት የጊዜ ገደብ ውስጥ (1990-2000) ብቻ አስራ ስድስት አሰልጣኞች መሾማቸውን ጠቅሷል፡፡

በዚህ ሁሉ የትውልድ ቅብብል ውስጥ በሁለቱም የሀገሪቱ ሊግ እርከኖች እየዋለለ አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ እያለ እዚህ የደረሰው አንጋፋው ክለብ ዘንድሮ ግን የዘመናት ልፋቱ በሊግ ዋንጫ ለመደምደም በቅቷል። ያኔ አዝናኝ እግር ኳስ በሚጫወትበት ወቅት ‘ሊቨርፑል’ ፡ የእሁድ ፕሮግራም የሚል ቅጥያ የተሰጠው ቆይቶም ከዘመኑ በቀደመ አደረጃጀት በመዋቀሩ አንዴ ‘የፊውዳል ክለብ’ አንዴ ደግሞ የወዛደሩን ሞራል ለመንካት ነው ወይ ? የሚል የብዙሃኑ ካድሬዎች ትችት የወረደበት አንጋፋው ክለብ ድፍን ሀያ ሦስት ዓመታት ካለ ዋንጫ ከተጓዘ በኋላ ዘንድሮ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ባለ ክብር ለመሆን በቅቷል።