ኢትዮጵያ ቡና በአስገዳጁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መመሪያ ምክንያት ከአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ጋር በመለያየት ረዳት አሰልጣኙን በሀላፊነት ሾሟል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ባለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር እጅግ አስደናቂ የውድድር ዘመናትን ያሳለፈው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ከሰሞኑ ባወጣው የላይሰንስ አስገዳጅነት ህግ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለመቀጠል ቢስማማም የፌዴሬሽኑ አልቀበለም ባይነት በመጨረሻም ክለቡ ወደ አዲስ አሰልጣኝ ፊቱን እንዲያዞር በማድረግ ሦስተኛ ረዳት አሰልጣኙ እና የካፍ ቢ ላይሰንስ ባለቤቱ አብይ ካሳሁን የቀጣዩ ዓመት የቡናማዎቹ ዋና አሰልጣኝ እንዲሆን ተሹሟል።
ፓሽን ፣ አሰጌ እንዲሁም ሀሌታ በሚባል የታዳጊ ፕሮጀክት ቡድኖች ውስጥ ስልጠናን የጀመረው የቀድሞው የቦሌ ክፍለከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች አብይ ካሳሁን በመቀጠል የአዲስ አበባ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ፣ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድንም ውስጥ አሰልጥኖ አልፏል። ከያዝነው ዓመት አንስቶ በኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን ውስጥ ሦስተኛው ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ከሰራ በኋላ በዋና አሰልጣኝነት ክለቡ በዛሬው ዕለት በይፋ ሾሞታል።
