የተጠናቀቀውን ዓመት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሆነው የፈፀሙት በአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የስድስት አዳዲስ እና የአንድ ነባር ተጫዋቾችን ፊርማ አግኝቷል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ጥቂት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው እና የተጠናቀቀውን ዓመት ከሻምፒዮኑ ንግድ ባንክ በመቀጠል ሊጉን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማዎች ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአንድ ነባር ተጫዋችን ውል ደግሞ ማራዘማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ዮርዳኖስ ምዑዝ ሀዋሳን ተቀላቅላለች። የቀድሞዋ የሲዳማ ቡና ፣ ደደቢት ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ አጥቂ ያለፈውን ዓመት በምሰራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተጫወተች በኋላ ቀጣዩ መዳረሻዋ ሀዋሳ ከተማ ሆኗል። ሌላኛዋ ፈራሚ ቻይና ግዛቸው ነች። የቀድሞዋ የድሬዳዋ ከተማ አምና ደግሞ በአዳማ ከተማ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ የተጫወተችዋ ሁለተኛዋ የቡድኑ አዲሷ ተጫዋች ሆናለች።
ሦስተኛዋ ፈራሚ ሀዋሳን በመልቀቅ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አምርታ የነበረችው አማካዩዋ ቃልኪዳን ወንድሙ በድጋሚ ወደ አሳዳጊ ቤቷ ስትመለስ የቂርቆስ ክፍለ ከተማዋ ሁለገብ ተጫዋች ሀረገወይን አበራን ጨምሮ ቤቴልሄም መስፍን ተከላካይ ከአዲስ አበባ ከተማ እና በረከት ዘመድኩን ግብ ጠባቂ ከሲዳማ ቡና ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ናቸው።
በክለቡ በአማካይ ቦታ ላይ ከአራት ዓመታት በላይ ቆይታን ያደረገችው አማካዩዋ ቅድስት ቴቃም ለተጨማሪ ዓመት በቡድኑ ውሏ ተራዝሞላታል።