ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ አራት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ አራት ተጫዋቾችን አስፈረመ

አንጋፋዋን አማካይ ጨምሮ አራት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ሀዋሳ ከተማ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን በተጠናቀቀው ዓመት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማዎች በትላንትናው ዕለት ዮርዳኖስ ምዑዝ ፣ ሀረገወይን አበራ ፣ በረከት ዘመድኩን ፣ ቻይና ግዛቸው ፣ ቃልኪዳን ወንድሙ እና ቤቴልሄም መስፍንን በማስፈረም ወደ ዝውውሩ የገቡ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ አራት አዳዲስ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በመጨመር የአዳዲሶቹን ቁጥር አስር ማድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ብርቱካን ገብረክርስቶስ ከሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ በኋላ ሀዋሳ ከተማን በይፋ ተቀላቅላለች። ኤግልስ እና አዲስ ኮከብ ከተባሉ ቡድኖች በኋላ በደደቢት መለያ በ2004 በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ መካፈል የጀመረችው አንጋፋዋ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ በመቀጠል በዳሽን ቢራ በከፍተኛ ዝውውር አምርታ የተጫወተች ሲሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መለያ ደግሞ ላለፉት ሰባት የውድድር ዘመናት ያሳለፈችው እና በቅርቡ ከሉሲዎቹ ስብስብ ራሷን ያገለገለችው አማካይ ቀጣዩ መዳረሻዋ ሀዋሳ ከተማ ሆኗል።

ሌላኛዋ የሀዋሳ ፈራሚ በተመሳሳይ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ዙለይካ ጁሀድ ናት። በመቻል ቡድን ውስጥ የክለብ ህይወቷን የጀመረችው እና ዘለግ ባሉ ስድስት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነበረችው ተጫዋቿ ከአቃቂ ቃሊቲ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ካሳለፈችበት ልደታ ክፍለ ከተማ በኋላ ቀጣዩ ክለቧ ሀዋሳ ከተማ ሆኗል።

ሦስተኛዋ ፈራሚ ደግሞ ግዙፏ የአማካይ እና የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቿ መሠሉ አበራ ሆናለች። በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከተማ ፣ መቻል ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የ2017 ቆይታዋን በልደታ ያደረገችው ተጫዋቿ የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈን ጥሪ ተከትላ ሀዋሳ ደርሳለች። ሌላኛዋ በንግድ ባንክ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና መቻል የተጫወተችው አጥቂዋ ታደለች አብርሀም የሀዋሳ አዲሷ ተጫዋች መሆኗ ዕርግጥ ሆኗል።