በቪዛ ምክንያት ስብስቡ የተመናመነበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለተጨማሪ አምስት ተጫዋቾች ጥሪ አድርጓል።
በቀጣዩ ቅዳሜ በዩናይትድ ስቴትስ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ከስብስቡ ውጪ በሆኑ ተጫዋቾች ምትክ ለአዳዲስ ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጓል።
በስብስቡ ጥሪ ከተደረገላቸው 23 ተጫዋቾች ውስጥ 13 ተጫዋቾች ብቻ ቀርተው የነበር ቢሆንም ቀደም ብለን ከሰዓታት በፊት እንዳሳወቅናችሁ ጊት ጋትኮችን ምሽት ላይ ደግሞ ተጨማሪ 5 ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።
በዚህም መሠረት ከነዓን ማርክነህ፣ አንተነህ ተፈራ፣ አማኑኤል ኤርቦ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ሻሂድ ሙስጠፋ ሌሎች በአዲስ መልክ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች መሆናቸው ታውቋል።
በአጠቃላይ 20 ተጫዋቾችን ያካተተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስከ ማክሰኞ ሐምሌ 22 ዝግጅቱን ካከናወነ በኋላ በዛው ዕለት ምሽት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚያቀና ይሆናል።