ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ባህር ዳር ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል

ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ባህር ዳር ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል

በአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ የሚመሩት የግዮን ንግሥቶቹ የሦስት አዳዲስ እና የሦስት ነባር ተጫዋቾችን ፊርማ አግኝተዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ አንድ ጊዜ ወርደው በተመሳሳይ ለሁለት ጊዜ ደግሞ ወደ ሊጉ በማደግ ተሳትፎን እያደረጉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ መሪነት በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ላለመውረድ ካደረጉት ትንቅንቅ በኋላ በሊጉ መቆየታቸውን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎቻቸው ማረጋገጣቸው ይታወሳል። በ2017 የውድድር ዘመን ቡድኑ ውስጥ ክፍተት ያለበትን ቦታ ለመድፈን አሰልጣኟ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ስታስፈርም ቡድኑ የሦስቱን ነባር ኮንትራት ደግሞ አራዝሟል።

 

አንጋፋዋ የግብ ዘብ ማርታ በቀለ ከአምስት የውድድር ዘመናት በኋላ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ባህር ዳር አምርታለች። የቀድሞዋ የዳሽን ቢራ ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ዘለግ ካለው የኤሌክትሪክ ቆይታዋ በኋላ ቡድኑን በመልቀቅ አዲስ ክለብ ተቀላቅላለች።

ሌላኛዋ የቡድኑ ፈራሚ አማካዩዋ ቤዛዊት ተስፋዬ ናት። የቀድሞዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ መቻል እና እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሀዋሳ ከተማ አሳልፋ ቀጣይ መዳረሻዋን ባህርዳር አድርጋለች።

ተከላካዩዋ ማህደር ባየህም የትውልድ ከተማዋን ክለብ ተቀላቅላለች። በድሬዳዋ ከተማ ፣ ሀዋሳ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈችው የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ያሬድ ባየህ ታናሽ እህት ሦስተኛዋ የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ሆናለች።

ክለቡ ከሦስቱ አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የአምበሏ እና ተከላካዩዋ ቃልኪዳን ተስፋዬ ፣ የተከላካዩዋ አሶሬ አይሶ እና የአጥቂዋን አስቴር ደግአረገን ውል ለተጨማሪ አመት ውላቸውን አራዝሟል።