በዝውውር መስኮቱ ጠንካራ ተሳትፎን እያደረጉ የሚገኙት ባህርዳር ከተማዎች ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል::
በአሰልጣኝ ሰርክአዲስ እውነቱ የሚመሩት ባህርዳር ከተማዎች በ2017 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ካደረጓቸው 26 ጨዋታዎች 22 ነጥቦችን በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው። በውድድር አመቱ ካጋጠማቸው የውጤት ቀውስ ወጥተው ለቀጣዩ የውድድር አመት ተፎካካሪ ለመሆን ያስችላቸው ዘንድ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ያስፈረሙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን የግላቸው አድርገዋል።
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መጫወት የቻለችው እንዲሁም ያሳለፍነውን የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ማሳለፍ የቻለችው ተከላካዩዋ የውብዳር መስፍን አንድ አመት በሚቆይ ውል ውሃ ሰማያዊ ለባሾችን ተቀላቅላለች።
ሌላኛዋ ፈራሚ ሳሮን ሰመረ ስትሆን የዘንድሮውን የውድድር አመት በልደታ ክፍለ ከተማ ያሳለፈችው አጥቂዋ በአንድ አመት ውል ፊርማዋን ለባህርዳር አኑራለች። የክለቡንም የጎል ማግባት ችግር ትቀርፋለች ተብሎ ተስፋ ተጥሎባታል::