የዩጋንዳው ሻምፒዮን ካምፓላ ኩዊንስ ሁለት ኢትዮጵያዊያንን ተጫዋቾችን በይፋ አስፈረመ።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤል መሪነት በዩጋንዳ የሴቶች ሱፐር ሊግ አሸናፊ በመሆን በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ላይ ተካፋዩ ካምፓላ ኪዊንስ በማጣሪያው ውድድር ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ ከአሰልጣኙ ጋር በሉሲዎቹ ውስጥ አብረው መስራት የቻሉት ሁለት ኢትዮጵያዊያንን በይፋ በዛሬው ዕለት አስፈርሟል።
ማዕድን ሳህሉ የመጀመሪያዋ ፈራሚ ተጫዋች ሆናለች። የቀድሞዋ የጥረት ኮርፖሬት ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና መቻል የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በሀዋሳ ከተማ ለተከታታይ ካሳለፈችው ሁለት ዓመታት በኋላ ቀጣይ ማረፊያዋ የዩጋንዳው ክለብ ሆኗል። ሌላኛዋ ፈራሚ አጥቂዋ ቱሪስት ለማ ስትሆን በይርጋጨፌ ቡና ፣ ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማ ለተከታታይ አራት ዓመታት ደግሞ በሀዋሳ ከተማ መለያ ቆይታን ካደረገች በኋላ ቅጣትን በተጠናቀቀው ዓመት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይም ያስተናገደችው ተጫዋቿ የአሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤልን ስብስብ ተቀላቅላለች።
