ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 16 ዋንጫዎችን ያስገኙት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ ሁኔታ በክለቡ ለ16ኛ ተከታታይ ዓመት ለመቆየት ፊርማቸውን አኑረዋል።
ሐምሌ 24 2003 የተመሰረተውና ወዲያው በ2004 የአዲስ አበባ ዋንጫን አሸናፊ በመሆን በዛው ዓመት በኢትዮጲያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ደረጃን በመያዝ በማጠናቀቅ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እያስመዘገበ ያለውን እጅግ ስኬታማ ጊዜ “ሀ” ብሎ የጀመረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስረታው እስካሁኗ ጊዜ ድረስ በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እየተመራ በድምሩ 16 ዋንጫዎችን ማስመዝገቡ ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፊት በአዲስ አበባ የፕሮጀክት ቡድን፣ ፀደይ የወንዶች ቡድን፣ ምስራቅ ሃረር የሴቶች ቡድን፣ ወወክማ፣ ወሴክማ፣ የካ ክ/ከተማ የሴቶች ቡድን እና ሴንትራል የጤና ኮሌጅን ያሳለፉት አሠልጣኝ ብርሃኑ ከ2003 ጀምሮ ያለፉትን 14 ዓመታት በባንክ ቤት ቆይታን አድርገው 16 ዋንጫዎችን ለክለቡ ያስገኙ ሲሆን አሁንም ዳጎስ ካለ ጥቅማጥቅም ጋር ለተጨማሪ 2 ዓመታት በቡድኑ ለመቆየት ፊርማቸውን አኑረዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዋና አሠልጣኙ በተጨማሪ የረዳቱን አሠልጣኝ ሽመልስ ጥላሁን እንዲሁም የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ንጉሴ ወልደአማኑኤል ውል ለተጨማሪ ዓመታት ማራዘሙም ታውቋል።