ኢትዮጵያን ወክለው በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፉት የጦና ንቦች የወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል አድሰዋል።
ከቀናት በፊት የዮናታን ኤልያስ እና መሳይ ሠለሞንን ውል ለማደስ እንደተስማሙ በገጻችን የተገለጹት ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳን የአሰልጣኝ ቅጥር ይፋ ያላደረጉ ቢሆንም ከፊታቸው ላለባቸው የካፍ ኮንፌዴሬሽን አህጉራዊ ውድድር እንዲሁም ለመጭው ዓመት የውድድር ዘመን ይረዳቸው ዘንድ የሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል በዛሬው ዕለት አራዝመዋል።
ከወላይታ ድቻ የታዳጊ ቡድን የተገኘው እና ያለፉትን ስድስት አመታት ዋናውን ቡድን ማገልገል የቻለው እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ሀገሩን ወክሎ መጫወት የቻለው ግብጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ነው።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ መድን መጫወት የቻለው እና ወደ ቀድሞ ክለቡ በመመለስ ማገልገል የቻለው አጥቂው ያሬድ ዳርዛ ሌላኛው ውሉን ያራዘመ ተጫዋች መሆን ችሏል።