በስምምነት ለመለያየት የታሰበው የፋሲል ከነማ እና የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጉዳይ እልባት አለማግኘቱ ተሰምቷል።
ከ2016 ጀምሮ ለሦስት ዓመታት በቡድኑ ለመቆየት ውል ያሰሩት ፋሲል ከነማዎች እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ያለፉትን ሁለት ዓመታትበብረው ሲሰሩ ቆይተው በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጨረሻ ላይ የአንድ ዓመት ቀሪ ውል እያላቸው በስምምነት ለመለያየት መቃረባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አስነብባ ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ ከተጠናቀረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሁለቱ መካከል የተደረገ ለመለያየት የሚያስችል ስምምነት የለም። ይህን ተከትሎ አሰልጣኝ ውበቱ አሁንም የዐፄዎቹ አሰልጣኝ ናቸው ማለት ነው። ፋሲል ከነማ ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር በስምምነት ለመለያየት እንደሚፈልግ ለአሰልጣኙ በግልፅ እንደተናገረ እና አሰልጣኝ ውበቱም ጥያቄው ከእነርሱ ከመጣ ለመለያየት ዝግጁ መሆናቸውን እና ክለቡ ማሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው በቀጠሮ ቢለያዩም እስካሁን ለመለያየት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ፋሲል ከነማዎች ቀጣዩን የቡድናቸውን አለቃ ለመሾም ስማቸው ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሲያያዝ ሰንብቶ አሁን ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር አብሮ ለመስራት መስማማታቸውን አስቀድመን ባደረስናችሁ መረጃ ገልፀን ነበር። ሆኖም የአሰልጣኝ ዮሐንስን ስምምነት በውል ለማሰር ዐፄዎቹ እክል ገጥሟቸዋል ምክንያቱ ደግሞ ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር ያለው ውል ባለመቀደዱ ነው።
በቀጣይ ቀናት በአሰልጣኝ ውበቱ እና በፋሲል መካከል ያለው ሁኔታ በምን መልኩ ይቋጫል የሚለው ተጠባቂ ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ በሀገረ አሜሪካ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የነበራቸውን የዕረፍት ጊዜ አጠናቀው ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸውን ሰምተናል።