ሶከር ኢትዮጵያ በብቸኝነት ባገኘችው መረጃ አንድ የሀገራችን የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ ሊጉን በቀጥታ ለማስተላለፍ ጨረታው ላይ መሳተፉ ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያለፉትን አምስት ዓመታት የምስል መብቱን ለመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ በመሸጥ የሊጉ ጨዋታዎች በዲ ኤስ ቲቪ የሱፐር ስፖርት ቻነሎች ለአድማጭ ተመልካቾች ሲደርሱ መደረጉ አይዘነጋም። አክሲዮን ማኅበሩ ከመልቲቾይዝ ጋር ያደረገው ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጣዮቹ ዓመታት ሊጉን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ዐየር ላይ ለማዋል ኮሚቴ በማዋቀር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከሰሞኑም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች የሀገራችን ታላላቅ የቴሌቪዥን ኩባንያዎች በጨረታው እንደሚሳተፉ ሲገለፅ እንደነበር አስተውለናል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቴሌቪዥን ተቋማት ጨረታው ላይ እንዲሳተፉ በውስን የጨረታ ሂደት ክፍት አድርጎ የቆየው የሰነድ ማስገቢያ ቀን ከትናንት በስትያ የተጠናቀቀ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም በጨረታው ላይ የተሳተፉ ተቋማት እነማን እንደሆኑ ለማጣራት ሞክራለች። የዝግጅት ክፍላችን ከመረጃ ምንጮቿ ባገኘችው መረጃ መሰረትም በጨረታው አስፈላጊውን ሰነድ በማስገባት ተጫራች ሆኖ የቀረበው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) መሆኑን አውቃለች።
በጉዳዩ ላይ ማረጋገጫ እንዲሰጡን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በኩል ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለአሁን ያልተሳካ ሲሆን በቀጣይ በጉዳዩ ዙሪያ የሚፈጠሩ አዳዲስ ጉዳዮችን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።