አስቻለው ታመነ አዲስ ክለብ ለማግኘት ተቃርቧል

አስቻለው ታመነ አዲስ ክለብ ለማግኘት ተቃርቧል

ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦሩ ቆይታ የነበረው ተከላካይ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

ቀደም ብለው የአብሥራ ሙሉጌታ ፣ ሬድዋን ሸረፍን ፣ አቤል ነጋሽን እና ጃዕፋር ሙደሲርን በማስፈረም የአማካዩ አቤል አሰበን ውል ያራዘሙት በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት ድሬደዋ ከተማዎች አሁን ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመቻል ቆይታ የነበረውን አስቻለው ታመነን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በ25 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2055′ ደቂቃዎች ጦሩን ማገልገል የቻለው ተጫዋቹ ከመቻል ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ስሙ በርከት ካሉ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ቢቆይም በስተመጨረሻ ብርቱካናማዎቹን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

በሁለት አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ያገኘው እና ከዲላ ከተማ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው የመሐል ተከላካዩ ደደቢትን ለቆ በ2007 ክረምት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ በኋላ ባለፉት ዓመታት
በወጥነት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ስኬታማ ቆይታ ካደረገ በኋላ በፋሲል ከነማ ፣ በመቻል እንዲሁም በብሔራዊ ቡድኑ አንበል ሆኖ መጫወቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ወደ ምስራቁ ክለብ ለማምራት ከጫፍ ደርሷል።