የሸገር ደርቢ በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

የሸገር ደርቢ በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ከ17 ሺህ በላይ ደጋፊዎች በታደሙበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአቤል ያለው ብቸኛ ጎል ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 መርታት ችሏል።


ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ሕዳሴ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ ሁለቱ ቡድኖች የተገናኙ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 አሸናፊነት መጠናቀቁ የሚታዎስ ነው። በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት በድጋሚ ሁለቱ ቡድኖች መገናኘት ችለዋል። ጨዋታውም ቀን 9:00 ሲል በሁለቱም ክለቦች ብዛት ባላቸው ደጋፊዎች ሕብረ ዜማ ታጅቦ በእጩ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት ጨዋታው ተጀምሯል።

ጨዋታው በጅማሮው በሙከራ የታጀበ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ሲሆን በ2ኛው ደቂቃ አቡበከር አዳሙ ከቅጣት ምት ባደረገው እና ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ በመለሰው ግሩም ሙከራ እንዲሁም  በ3ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ኳሱን ገፍቶ በመግባት ከግብ ጠባቂው ጋር መገናኘት ቢችልም ኳሱ በዳንላንድ ኢብራሂም ግብ ከመሆን ድኗል።

ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ጥቃት ለማድረስ ጥረቶችን ማድረግ ሲችሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አጥቂዎችን ዒላማ ያደረጉ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ የአየር ላይ ኳሶችን ሲጠቀሙ በተቃራኒው ቡናዎች ኳስን መስርተው በመግባት ብርቱ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። ነገር ግን በአጋማሹ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ  ጫና ፈጥሮ በመጫወቱ ረገድ በመጠኑ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ ነበሩ። በጨዋታው 53ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዳንላንድ ኢብራሂም አቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከ ሜዳ ተሰናብቷል ፤ የእርሱን ቦታ በመተካትም ግብ ጠባቂው እንዳሻው እሸቴ ተቀይሮ ገብቷል።

ያገኙትን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም አብዝተው ጫና መፍጠር የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የድካማቸውን ፍሬ ያገኙበትን ግብ አስቆጥረዋል። 66ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ከቀኝ መስመር ከቢኒያም ፍቅሬ የተቀበለውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አቤል ያለው አመቻችቶ ያቀበለው ሲሆን አቤል ያለው ኳሱን ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

በመጨረሻ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ውጥረት የሞላባቸው እንቅስቃሴዎች የተመለከትን ሲሆን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 84ኛው ደቂቃ ላይ በቢኒያም ፍቅሩ እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በአቤል ያለው አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ጠባቂው እንዳሻው ይዟቸዋል።


ቡናማዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ፈረሰኞቹ በአንጻሩ በአፈወርቅ ኃይሉ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው እንዳሻው እሸቴ አግዶበታል። ይህም የመጨረሻው ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።