በአዲስ አበባ ስቴዲየም የተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

በአዲስ አበባ ስቴዲየም የተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛው ሳምንት የምድብ አንድ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ

7፡00 በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ማራኪ ፉክክር የታየበት ቢሆንም ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአጋማሹ የተሻለ ብልጫ በነበራቸው በባህርዳር ከተማዎች በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባር ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በአዞዎቹ በኩል ደግሞ ይገዙ ቦጋለ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ሁለተኛው አጋማሽ ከእንቅስቅሴ በዘለለ የጠሩ ሙከራዎች አልተደረገበትም። ቡድኖቹ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ ከቆዩ በኋላም በ74’ደቂቃ ላይ ታምራት እያሱ ከይሁን እንዳሻው የተሻገረለት ኳስ በማስቆጠር አዞዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም ጫና ሲፈጥሩ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ግብ አስቆጥረዋል። መሳይ አገኘሁ ከማዕዝን አሻግሯት ግርማ ዲሳሳ በግሩም ቮሊ ያስቆጠራት ግብም ባህርዳር ከተማን አቻ ማድረግ የቻለች ግብ ነች። ከግቧ በኋላም ግርማ ዲሳሳ ግብ አስቆጥሮ መለያውን በማውለቁ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ


የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ
ጥቂት የግብ ሙከራዎች እንዲሁም ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። በአጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ዘጠኝ የሚደርሱ ሙከራዎች ቢደረጉም በኤሌክትሪክ በኩል አብነት ተስፋዬ በደረቱ አብርዶ ከሞከራት ኳስ እና በነብሮቹ በኩል ተመስገን ብርሀኑ ከመስመር አሻግሯት ብሩክ በየነ በግንባር ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ አልተደረገበትም።

በኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻለ ብልጫ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ መጠነኛ ለውጥ የታየበት ቢሆንም የተደረጉት ሙከራዎች ግን ጥቂት ነበሩ።  ፀጋአብ ግዛው ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራ እንዲሁም እዮብ ገብረ ማርያም ከግራ መስመር አሻግሯት የነብሮቹ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ኳስም እንዲሁም በሌላ አጋጣሚ ሞከራት ግብ ጠባቂው ያወጣት ተጨማሪ ኳስ የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም ከመስመር በረዥሙ ተሻግራ ፀጋአብ ግዛው ያልተጠቀመባት አስቆጪ ሙከራ ነብሮቹን ባለ ድል ለማድረግ ተቃርባ ነበር። ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።