በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛው ሳምንት የምድብ ሁለት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ መቻል

በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ ጨዋታ የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ መቻሎች በሁሉም ረገድ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ሆኖም በ16ኛው ደቂቃ ኪቲካ ጅማ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ በመምታት ያስቆጠራት ግብ መቐለ 70 እንደርታዎችን መሪ ማድረግ ችላለች። ሆኖም መሪነቱ የቆየው ለአንድ ደቂቃ ብቻ ነበር፤ በ17ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አበራ አሻግራት አብዱልከሪም ወርቁ ያስቆጠራት ኳስ ጦሩን አቻ ማድረግ ችላለች። ከግቧ በኋላም በማጥቃቱ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በ19ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አበራ በጥሩ መንገድ አሻግሯት ቸርነት ጉግሳ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቦቹ በኋላ መቻሎች በመሐመድ አበራ አማካኝነት መቐለ 70 እንደርታዎች ደግሞ በቦና ዓሊ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም መሐመድ አበራ ሞክሯት ሶፎንያስ ሰይፈ ያዳናት ኳስ የጦሩን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የመቻሎች እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘበት መቐለዎች ደግሞ የተሻለ የተነቃቁበት ነበር። በመቻል በኩል ዳዊት ማሞ በመቐለ በኩል ደግሞ ፍፁም ዓለሙ ያደረጉት ሙከራም ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በ64′ ደቂቃም ሱሌይማን ሐሚድ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ከመለሳት በኋላ ፍፁም ዓለሙ ወደ ግብነት በቀየራት ግብ መቐለ 70 እንደርታዎች አቻ መሆን ችለዋል። ከግቧ በኋላ መቻሎች ተጭነው መጫወት ቢችሉም የመቐለ 70 እንደርታ ተከላካዮች አልፈው ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሽረ ምድረ ገነት

በአንፃራዊነት ሽረ ምድረ ገነቶች የተሻለ ብልጫ በወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ቢሆንም የተፈጠሩት ዕድሎች ግን በጥራት ከፍ ያሉ ነበሩ። ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች የተሻለ ጫና በፈጠሩት ሽረ ምድረ ገነቶች በኩል ዳንኤል ዳርጌ ከበኃይሉ ግርማ የተላከችለትን ኳስ ተጠቅሞ ያመከናት አስቆጪ ሙከራ ተጠቃሽ ስትሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩልም በጨዋታው ጅማሮ ብሩክ ብፁዕአምላክ በግንባር ሞክራት ግብ ጠባቂው እንደ ምንም ወደ ውጭ ያወጣት ድንቅ ሙከራ እንዲሁም ሳይመን ፒተር ከሳጥን ውጭ ያደረጋት ጥሩ ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ በረዣዥም ኳሶች እና በሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን አጨዋወቶች ቢታጀብም ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በሽረ ምድረ ገነት በኩል ስንታየሁ ዋለጬ ከቅጣት ምት ያደረጋት ጥሩ ሙከራ እንዲሁም ሽመክት ጉግሳ አክርሮ የሞከራት ኳስ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ዘላለም አበበ በረዥሙ አሻግሯት ግብ ጠባቂው እንደ ምንም ያወጣት ኳስ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም ተስፋዬ ታምራት ከቆመ ኳስ አሻግሯት አስጨናቂ ፀጋዬ በግንባር ገጭቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት አስቆጪ ሙከራ ሀምራዊ ለባሾቹን ባለ ድል ለማድረግ ተቃርባ ነበር። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

