የሮድዋ ደርቢ በያሬድ ባየህ ብቸኛ ግብ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል
ከቀኑ 10:00 ሰዓት ሲል የተጀመረውና በሊጉ ለ30ኛ ጊዜ የተካሄደው ሮድዋ ደርቢ ሁለት የተመሳሳይ ከተማ ክለብ የሆኑትን ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን በደጋፊዎቻቸው ፊት አገናኝቷል። ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያ ጨዋታቸው ድል ያደረጉበትን የማሸነፍ ስሜት ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር አስመልክተውናል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሲሆን በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። 7ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ደግፌ አለሙ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል። ይህም ለሲዳማ ቡናዎች እጅግ አስቆጪ ሙከራ ነበር። በተቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ምንም አይነት ሙከራ ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ልፋታቸው ፍሬ ያፈራበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ተጫዋች ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ ምክንያት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት አምበሉ ያሬድ ባየህ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በሀዋሳ ከተማ በኩል በእስራኤል እሸቱ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ሊጉን መምራት ጀምሩዋል።

