4ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል
አርባምንጭ ከተማ ከ አዳማ ከተማ
በውድድር ዓመቱ ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ አንድ ነጥብ መሰብሰብ የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ለማስመዝገብ አዳማ ከተማን ይገጥማሉ። በዛሬው ጨዋታ ድል ካደረጉ የአራት ደረጃዎች መሻሻል የሚያገኙት አዞዎቹ ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በመጨረሻው ጨዋታ ዋጋ ያስከፈላቸውን ግለ ሰባዊ ስህተት ማረም እንዲሁም የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ መሻሻል ይኖርባቸዋል።
በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የባዶ ለባዶ ውጤት ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች ከተከታታት የአቻ ውጤቶች በኋላ ድል ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ በተከታታይ መርሐ-ግብሮች መረቡን በማስከበር በመከላከሉ ረገድ አወንታዊ ነገር ማስመልከት ቢችልም በማጥቃቱ በኩል ያለውን ድክመት መቅረፍ ዋነኛ የቤት ስራው መሆን ይኖርበታል። በተለይም ከሀድያ ሆሳዕና ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ የነበረው ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ያልፈጠረ የማጥቃት አጨዋወት ማሻሻል በዋነኝነት ከቡድኑ ይጠበቃል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል አሸናፊ ተገኝ፣ በኃይሉ ተስፋዬ፣ አንዷለም አስናቀ እና በርናንድ ኦቼንግ በጉዳት እንደማይሰለፉ ሲታወቅ ይገዙ ቦጋለም መጠነኛ ጉዳት አስተናግዷል፤ ሆኖም በጨዋታው የመሳተፉ ዕድል ሰፊ ነው። በአዳማ ከተማ በኩል አላዛር ሽመልስ፣ ዳዋ ሆቴሳ፣ ማይክል ኪፕሩቪና ሚካኤል ሰፋ፣ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ ነቢል ኑሪና ቢንያም አይተን ግን ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በተጨማሪም ጉዳት ላይ የነበረው ሚራጅ ሰፋ ልምምድ መጀመሩን ሰምተናል።
ቡድኖቹ የቀድሞ የአርባምንጭ ከተማና በአሁን ወቅት በአዳማ ከተማ የሚገኘው አሕመድ ሑሴን ሀትሪክ የሰራበት የመጨረሻው ግንኙነት ጨምሮ በሊጉ 18 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 8 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ 4 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አርባምንጭ 17 አዳማ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ በመቻል ሽንፈት ያስተናገዱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሽንፈቱ አገግመው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ። እስካሁን ድረስ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ሀምራዊ ለባሾቹ ከሁሉም በላይ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ያለን ቡድን እንደመግጠማቸውም ከፊት መስመሩ ባሻገር በሁሉም ረገድ መሻሻል ግድ ይላቸዋል።
በሀዋሳ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው ተከታታይ ድሎች ያሳኩት ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን ዘጠኝ አድርሰው ብያንስ ሁለት ደረጃዎች ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። መቐለ 70 እንደርታን ባሸነፉበት ጨዋታ ከመመራት አንሰራርተው ሦስት ነጥብ ያሳኩት ብርቱካናማዎቹ ድል ባደረጉባቸው ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ማስቆጠራቸው በጥሩ ጎኑ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም የግብ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ከዚህም በላይ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 16 ጊዜ ሲገናኙ ድሬዳዋ ከተማ 6 ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 5 ጊዜ ድል አድርገዋል፤ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 31 ጎሎች በተቆጠሩበት የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ 2 ጊዜ ብቻ ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲሆን ባንክ 16፣ ድሬ 15 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ጉዳት ላይ ካለው ካሌብ አማንካዋህ ውጭ ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው፤ ድሬዳዋ ከተማዎችም ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው ለጨዋታው ይቀርባሉ።
ወልዋሎ ከ መቻል

ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸውን ያሳኩት ወልዋሎዎች በ2017 ዳግም ወደ ሊጉ ከተመለሱ በኋላ ከ 36 የጨዋታ ሳምንታት ቆይታ ከሰንጠረዡ ግርጌ መላቀቅ ችለዋል። መቻልን በሚገጥሙበት የዛሬ ጨዋታ ደግሞ የዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ለማግኘት እንደሚያልሙ እሙን ነው። ሆኖም በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ያስተናገደው የኋላ ክፍላቸው እንዲሁም አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለው የፊት መስመራቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል።
ሁለት ድሎች እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በድምሩ ሰባት ነጥቦች የሰበሰቡት መቻሎች በዛሬው ጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ በሆነ ልዩነት ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሊጉን መሪነት ይረከባሉ። በሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ጠንካራ የፊት መስመር ያላቸው መቻሎች የተጠቀሰውን ጥንካሬ ማስቀጠል ቀዳሚ የቤት ስራቸው ነው። ቡድኑ በነገው ዕለት ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም ለወትሮ የመከላከል አደረጃጀቱ ማሻሻል ግን ምናልባትም አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረትን የሚያሳስባቸው ብቸኛው ነገር ይመስላል።
በወልዋሎ በኩል አጥቂው ኮንኮኒ ሐፊዝ በገጠመው መጠነኛ ጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው፤ በመቻል በኩል ደግሞ ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጋናዊው ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከክፍያ ስርዓቱ ህግ ጋር ተያይዞ ወደ ሀገሩ መመለሱንና ከዚህ በኋላ ለመቻል ግልጋሎት እንደማይሰጥ ታውቋል።
በፕሪምየር ሊጉ 6 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱም ክለቦች መቻል 3 ጊዜ ድል ሲቀናው ወልዋሎ 2 ጊዜ አሸንፏል፤ በአንዱ ደሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹም መቻል 6 ወልዋሎ ደግሞ 3 ግቦች አስቆጥረዋል።

