በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚደረጉ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀዲያ ሆሳዕናን 3ለ1 ካሸነፉበት የውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ ተከታታይ ሦስት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት የጣና ሞገዶቹ በሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ጎሎችን ባያስተናግዱም የነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ግን ደጋፊዎች ላይ ስጋትን ጭሯል። ሆኖም እንደ አዲስ የተዋቀረው ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ እንቅስቃሴውን በቶሎ የማያሻሽል ከሆነ እንዳለፉት ዓመታት ለዋንጫ መፎካከር ቀላል ላይሆንለት ይችላል።
ባሳለፍነው ሳምንት በሸገር ከተማ የውድድሩን የመጀመሪያ ሽንፈት ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ በቀጣዩ ሽግሽግ ምክንያት ደግመው እስኪመለሱ ድረስ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት የሚያደርጉትን የመጨረሻ ጨዋታ በድል ለማሳካት ከባድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ አጥተውት የነበረውን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት በዛሬው ጨዋታ መልሰው ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ከጨዋታው ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ።
ባህር ዳር ከተማ ክንዱ ባየልኝ እና ወሳኙን የግብ ዘብ ፔፔ ሰይዶ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አያገኝም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 12 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ አራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት ድሎችን አሳክተው ስድስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ አሥራ አንድ ባህር ዳር ከተማ አሥራ ሦስት ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ምድረገነት ሽረ ከ ሲዳማ ቡና
መቐለ 70 እንደርታን አሸንፈው በጥሩ ሁኔታ ውድድሩን ቢጀምሩም ቀጥለው ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኙት ምድረገነት ሽረዎች በመከላከሉ አንድ ጎል ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ አደረጃጀት ቢኖራቸውም በተቃራኒው ግን በማጥቃቱ በኩል በአራት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ማስቆጠሩ ትልቁ ድክመቱ ነው።
በፋሲል ከነማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጪ ያደረጓቸውን ሌሎች ሦስት ጨዋታዎች በድል የተወጡት ሲዳማ ቡናዎች በቀጣዩ ሽግሽግ ምክንያት ደግመው እስኪመለሱ ድረስ በመቀመጫ ከተማቸው የሚያደርጉትን የመጨረሻ ጨዋታ በድል መወጣት ለአዲስ አበባ ቆይታቸው የሚፈጥርላቸው በራስ መተማመን ቀላል የሚባል አይደለም።
በሽረ ምድረ ገነት በኩል ቢኒያም ላንቃሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም ፤ ሕመም ላይ የሰነበተው ፀጋአብ ዮሐንስም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በሲዳማ ቡና በኩል አበባየሁ ሀጂሶ በጉዳት ደግፌ ዓለሙ ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።
ቡድኖቹ በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ሦስቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ስድስት ሲያስቆጥር ሽረ ደግሞ ሦስት ማስቆጠር ችሏል (የተሰረዙትን የ2012 ሁለት ጨዋታዎች አያካትትም)።
ኢትዮጵያ መድን ከ አርባምንጭ ከተማ
ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ መልስ ከሀዲያ ጋር በነበረውና በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ማራኪ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ 2ለ1 ያሸነፉት ኢትዮጵያ መድኖች ከሁለት ጨዋታዎች የሰበሰቧቸው አራት ነጥቦች ከነበረባቸው የውድድር መደራረብ አንጻር መልካም የሚባሉ ናቸው። የዓምናው ቻምፒዮን በርካታ ተጫዋቾችን ቢለቅም እንደ አዲስ የተወሃዳበት ፍጥነት ብዙዎችን አስገርሟል።
ደካማ የሚባል አጀማመር ያደረጉት አርባምንጭ ከተማዎች በሊጉ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ቢለያዩም በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ያስተናገዷቸው ሽንፈቶች ከደጋፊዎች መጠነኛ ቅሬታ አስነስተዋል። ቡድኑ በተለይም የሚታወቅበትን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እያጣ መምጣቱ ትልቁ ትኩረት ሊሰጡበት የሚገባው ነው።
በኢትዮጵያ መድን በኩል ግብጠባቂው አቡበከር ኑራ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን በረከት ካሌብ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በአርባምንጭ ከተማ በኩል አሸናፊ ተገኝ ፣ በኃይሉ ተስፋየ ፣ አንዷለም አስናቀ እና በርናንድ ኦቼንግ አሁንም በጉዳት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ሲሆኑ አሸናፊ ፊዳ በቅጣት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል እንዲሁም ይገዙ ቦጋለ በሕመም ምክንያት የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።
ድሬዳዋ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ውድድሩን በሀዋሳ ባስተናገዱት ሽንፈት ቢጀምሩም ቶሎ በማገገም ወላይታ ድቻ እና መቐለ 70 እንደርታን ያሸነፉት ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻው ሳምንት ግን በንግድ ባንክ የ2ለ0 ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ከእንቅስቃሴ አንጻር ጥሩ የሚባለው ቡድኑ በየዓመቱ ከሚገጥመው የውጤት ውጣውረድ ለማምለጥ ወደ ማሸነፍ መመለሱ የግድ ይለዋል።
እንዳለፈው ዓመት ሁሉ እጅግ ደካማ አጀማመር እያደረጉ የሚገኙት ወልዋሎ ዓ/ዩዎች እስካሁን ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፈው አንድ አቻ ብቻ አስመዝግበዋል። ሆኖም በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ቡድኑ እንደ አዲስ የተገነባ ቢሆንም ቶሎ ተቀናጅቶ ወደ ውጤቶ መመለሱ ግን አፍታ የማይሰጠው ሥራ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይ ሲሆን በ2 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ወልዋሎ የዓምናውን የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ብቻ አሸንፏል። በአምስቱ ግንኙነቶች ድሬዳዋ 8 ፣ ወልዋሎ 5 ጎሎች አስቆጥረዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል መጠነኛ ጉዳት ላይ የሚገኘውን ተከላካይ አስቻለው ታመነን የማሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ሲገለጽ ሌሎቹ የቡድን አባላት ግን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። በወልዋሎ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።


