የ7ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እነሆ !
ወላይታ ድቻ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ 09፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም ይካሄዳል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በረዳት አሰልጣኛቸው አምጣቸው ኃይሌ እየተመሩ ሦስት ነጥቦችን ለማሳካት እጅግ ተቃርበው የኋላ የኋላ በተቆረጠረባቸው ጎል ከንግድ ባንክ ጋር 1ለ1 ተለያይተው ነጥብ የተጋሩት ወላይታ ድቻዎች በትናንትናው ዕለት የቀድሞ አሰልጣኛቸውን መሳይ ተፈሪን በዋና አሰልጣኝነት ሾመዋል። ሆኖም ቡድኑ ካለበት 19ኛ ደረጃ እና በስድስት ጨዋታዎች ካገኘው ሁለት ነጥብ በቶሎ ለማሻሻል የአሰልጣኙ መቀየር የሚፈጥረው ፈጣን መነሳሳት የሚጠበቅ ነው።
ያለፈው ዓመት የውጤት ማጣት ዘንድሮም በላያቸው ላይ እያንዣበበባቸው የሚገኙት ወልዋሎዎች የስነልቦና ጥንካሬያቸው ዘንድሮም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ቡድኑ ከምድረገነት ሽረ ጋር 0-0 ሲለያይ ካገኘው አንድ ነጥብ ውጪ በአምስቱ ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከዚህ የደረጃ ግርጌ ከፍ ለማለት እጅግ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል።

በወልዋሎ ዓ/ዩ በኩል ተከላካዩ ሄኖክ ገብረመድኅን እና አጥቂው ኢብራሂም መሐመድ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በወላይታ ድቻ በኩል ግን ከአሰልጣኙ ሹመት ውጪ አዲስ የተሰማ የቡድን ዜና የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 6 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ወላይታ 2 ጊዜ አሸንፎ 4 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸውም ወላይታ ድቻ 6 ወልዋሎ ዓ/ዩ 3 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ
በእኩል ነጥቦች በአንድ ግብ ልዩነት ተበላልጠው የተቀመጡ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ከተጠባቂ መርሐግብሮች መካከል አንዱ ነው።
ነጌሌ አርሲን በ83ኛ ደቂቃ ጎል እየመሩ ለማሸነፍ እጅግ ተቃርበው የነበሩት አዳማ ከተማዎች በ90+2ኛው 90+6ኛው ደቂቃ ጎሎችን አስተናግደው መሸነፋቸው ይታወቃል። ከዚህ ጨዋታ በፊት በተደረጉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ጎል ያላስተናገዱት አዳማዎች በዚህ ጨዋታ ላይ ያስተናገዱት ሽንፈት አስደንጋጭ ነበር። አሰልጣኝ ስዩም ከበደም በ6 ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ብቻ ማስቆጠር የቻለው የአጥቂ ክፍላቸው ላይ ማሻሻያ ማድረግ የመጀመሪያ ትኩረታቸው ይሆናል።
ከሦስት የአቻ እና አንድ ሽንፈት በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ የ2ለ0 ድል የተቀዳጁት ባህር ዳር ከተማዎች በዚህ ጨዋታ ላይ በሁሉም የሜዳ ክፍል የነበራቸው ተነሳሽነት እና ብልጫ ግሩም ነበር። እጅግ በተደጋጋሚ የሚነገረው የቡድኑ የወጥነት ችግር ላይ ማተኮር እና ተከታታይ ድሎችን ለማስመዝገብ ማለም የአሰልጣኞች ደግአረገ ይግዛው የመጀመሪያ እርምጃ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
በአዳማ ከተማ በኩል ጋዲሳ ዋዶ በባህር ዳር ከተማ በኩል ደግሞ ከጉዳቱ እያገገመ የሚገኘው ክንዱ ባየልኝ በጨዋታው ላይ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 12 ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 7 በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አዳማ 4 አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። ባህር ዳር 13 ሲያስቆጥር አዳማ 8 አስቆጥሯል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ነጌሌ አርሲ

ሁለት ከድል የተመለሱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ2 አሸንፈው የመጡት ኢትዮጵያ መድኖች በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ 3ለ0 መምራት በቻሉበት እንቅስቃሴ ግሩም ነበር። በሊጉ ካስቆጠሯቸው አምስት ግቦች 60% የሚሆነውን ባስቆጠሩበት የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ከዕረፍት መልስ ጫና ተፈጥሮባቸው ሁለት ጎሎችን ቢያስተናግዱም በርካታ የማጥቃት ሽግግሮችን በመመከት ትልቅ ድል ማሳካታቸው ለዛሬው ጨዋታ የሚፈጥረው መነሳሳት ቀላል አይደለም።
በፕሪሚየር ሊግ ታሪካቸው የመጀመሪያ ድል ያሳኩት ነጌሌ አርሲዎች በአዳማ ከተማ 83ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረባቸው ጎል ለመሸነፍ ተቃርበው በ90+2 እና 90+6ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች እጅግ ጣፋጭ ድል አሳክተዋል። በራሳቸው ስህተቶች ሽንፈቶችን ሲያስተናግዱ የነበሩት ሰጎኖቹ አሁን ላይ ግን በራስ መተማመናቸውን መለሰው ያገኙ ይመስላሉ። ሆኖም ተጋጣሚያቸው የዓምናው ቻምፒዮን ኢትዮጵያ መድን መሆሁ ግን ለዛሬው ጨዋታ የሚሰጣቸው የቤት ሥራ ፈታኝ ሊሆን ይችላል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በነገሌ አርሲ በኩል በረከት ወልዴ እና አብዱልባሲጥ ከማል በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ይህ ግንኙነት ለሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ የመጀመሪያው ነው።

